በህገ ወጥ መንገድ የተገኙ 36 ሽጉጦችና ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

75

ነቀምቴ ፤ ሚያዝያ 09/2013 (ኢዜአ) በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በህገ ወጥ መንገድ የተገኙ 36 ሽጉጦችና ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች ከተተኳሽ ጥይቶች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ሳጂን ወንድሙ ዋቅወያ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  የጦር መሳሪያዎቹ የተገኙት ሚያዝያ 05/2013ዓ.ም  በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ ወረዳ አገምሳ ኬላ በተደረገ ፍተሻ ነው።

በመለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ በህገ ወጥ መንገድ ተጭነው ሲጓጓዙ  ከተገኙት የጦር መሳሪዎች መካከል ሶስት ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ፣ 33 ቱርክ ሰራሽና ማካሮቭ ሽጉጦች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እንዲሁም ከ15ሺህ በላይ የተለያዩ ተተኳሽ ጥይቶች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን  ዋና ሳጂን ወንድሙ ገልጸዋል።

መሳሪያዎቹ በኬሻ ተጠቅልለው ለቱሉ ጋና፣ ነቀምቴ እና ጉቲን አካባቢዎች ተብለው በአድራሻ የተላኩ መሆናቸውን ያስረዱት ዋና ሳጂን ወንድሙ፣ የጦር መሳሪዎቹን ጭኖ የነበረው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን አስረድተዋል።

ሕገ ወጥ መሳሪያዎቹ በቁጥጥር የዋሉት የፌዴራል ፖሊስ ፣የፀረ ሽብር ግብረ ሃይልና የአሙሩ ወረዳ መደበኛ ፖሊስ በጋራ ባደረጉት የተቀናጀ ትብብር መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም