የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከ300 ለሚልቁ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

54

ሚያዚያ 9 ቀን 2013 (ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከ300 በላይ ለሚሆኑ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ።

ታራሚዎቹ ከእስር ጊዜ ፍርዳቸው አንድ ሶስተኛውን የጨረሱ መሆናቸው ተገልጿል።

ይቅርታውን ያገኙት ስርቆት፣ ድብደባ ግድያና ሌሎች ወንጀሎችን ፈፅመው ከወራት እስከ 20 ዓመታት የእስር ፍርደኛ የነበሩ ታራሚዎች ናቸው።

ከነዚህም መካከል በመተከል ዞን ግልገል በለስ ማረሚያ ቤት የነበሩ 124 ታራሚዎች ዛሬ ከእስር ተለቀዋል።

የዞኑ ኮማንድ ፖስት ወታደራዊ መኮንኖችና የፍትህ አካላት በተገኙበት ለታራሚዎቹ ትምህርትና ምክር ተሰጥቷቸዋል።

የመተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ዳምጤ ሊዴ ይቅርታው ለረጅም ጊዜ ይቅርታ የሚቀርብበት አንድ ሶስተኛ የተሰኘው የይቅርታ መመሪያ ገቢራዊ የተደረገበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለያዩ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው በማረሚያ ቤት የቆዩ ታራሚዎች ከእስር ወጥተው ማኅበረሰቡን ሲቀላቀሉ ሌሎችን ማስተማርና አምራች ዜጎች መሆን እንጂ ወደ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች መሰማራት እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።

ከእስር የተለቀቁት በፀጥታ ሁኔታና በእስር ቤት በነበራቸው ስነ ምግባር በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተለይተው ከእስር ጊዜ ፍርዳቸው አንድ ሶስተኛውን የጨረሱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም