በተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ 12 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደረሰ

88

አምቦ፣ሚያዚያ 09/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን ሊበን ጃዊ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ በ12 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው  ፖሊስ አዛዥ ተወካይ ዋና ሳጂን ሚልኪያስ ሃብቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አደጋው የደረሰው ትናንት በወረዳው ኮምቦሊቻ ሰደን  ቀበሌ ውስጥ ነው።

ከአምቦ 13 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ጌዶ ሲጓዝ የነበረ የታርጋ ቁጥሩ ቁጥሩ ኮድ 3– 29760 ኦሮ የሆነ ሚኒባስ ተሽከርካሪ መንገድ ላይ ከቆመ ሲኖትራክ ጋር በመጋጨቱ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል ።

በአደጋው የአሽከርካሪው ህይወት  ወዲውኑ ሲያልፍ  በ12ሰዎች ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡

ከበድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሰባት ሰዎች አምቦ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እርዳታ  እየተደረገላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ታክመው ወደየቤታቸው መሄዳቸውን ዋና ሳጂን ሚልኪያስ አመልክተዋል፡፡

የሟቹ አስክሬን ቤተሰቦቹ እንዲረከቡ መደረጉን ጠቁመው የአደጋው መንስኤ መንገድ ስቶ የቆመ ሲኖትራክ ወደ መንገዱ ለመመለስ እየተጎተተ እያለ ሚኒባሱ በመጋጨቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሚያዚያ 4/2013ዓ.ም በዚሁ አካባቢ በተፈጠረ የተሽከርካሪ አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም