ከስደት ተመላሽ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚተገበር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

85

ሚያዚያ 8 ቀን 2013 (ኢዜአ) የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንና ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ ከስደት ተመላሽ ሴቶችና ወጣቶችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ።

ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን እና የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ የኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሮል ዊልሰን የፕሮጀክቱን ማስጀመሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከውጭ አገራት የመጡ ከስደት ተመላሽ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ ያለው የስራ እድል ፍላጎትና አቅርቦት የተመጣጠነ አይደለም ያሉት አቶ ንጉሱ ይህን ለማሟላትና ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መንግስት ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ መኖሪያቸው ጎዳና የሆኑ ዜጎችን፣ ተፈናቃዮችና ከስደት ተመላሽ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ እደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በአገሪቷ በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ወደ ስራ ፈላጊነት ይገባሉ ያሉት አቶ ንጉሱ በመሆኑም ወደ ስራ ዓለም ለመቀላቀል የሚመጡ ወጣቶችን የስራ ባለቤት የማድረግ ስራ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።

የስራ አጥነት ችግሩን መፍታትና አካታች የስራ እድሎችን መፍጠርም ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ ከተለያዩ አገራት ስደት የተመለሱ 600 ሴቶችና ህጻናትን ለመደገፍና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።

እነዚህ ወገኖች በአገር ውስጥ የስራ እድል ቢመቻችላቸው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን ብሎም አገራቸውን በኢኮኖሚ የመደጎም ሚና እንዲጫወቱ የማድረግ ሚና ያለው መሆኑንም አክለዋል።

አቶ ንጉሱ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሴቶችና ወጣቶች በምልመላ፣ በስልጠናና በማደራጀት የማቋቋም ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ የኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሮል ዊልሰን በበኩላቸው፤ ድጋፉ ኢትዮጵያዊያኑን ከተለያየ ችግር ለመታደግ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በማቋቋም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ያስችላልም ብለዋል።

መሰል ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚተገበረው ፕሮጀክቱ በተለይም ከስደት ተመላሽ ዜጎች በብዛት በሚገኙባቸው በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችና በአዲስ አበባ 600 ሴቶችና ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

በኢትዮጵያ እንደ አ.አ.አ በ2030 ሃያ ሚሊዮን የስራ እድሎችን ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን በየዓመቱ ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ስለመሆኑ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም