የኮቪድ-19 መመሪያዎች አተገባበር ክትትልና ቁጥጥር አዎንታዊ ለውጥ እየተመዘገበበት ነው - ዶክተር ሊያ

73

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8 /2013 (ኢዜአ)  የኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያዎች አተገባበር ክትትልና ቁጥጥር አዎንታዊ ለውጥ እየተመዘገበበት መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶከተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፤ የበሽታው ስርጭትና ምጣኔ ግን አሁንም እየጨመረ ነው ብለዋል።

መመሪያው ተጠናክሮ ወደ ትግበራ በመግባቱ በአዲስ አበባና በክልሎችም ማስክ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንና ያለ ጥንቃቄ የሚካሄዱ ስብሰባዎች መቀነሳቸውን ገልፀዋል።

ዶክተር ሊያ በኮቪድ-19 መከላከልና መቆጣጠር ላይ ባተኮረው መግለጫቸው ቁጥጥሩ ከተጀመረ ወዲህ በአዲስ አበባ ከ73 ሺህ የሚበልጡ ግለሰቦች ማስክ ባለማድረግና አካላዊ ርቀት ባለመጠበቅ በፖሊስ ተይዘው አስተማሪ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ገልጸዋል።

ደንቦቹን ተላልፈው ለተገኙ ከ400 በላይ ድርጅቶች ሕጋዊ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን፤ 30 ግለሰቦችና 16 ድርጅቶችም ጉዳያቸው በሕግ በመታየት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በልዩ ሁኔታ መሰብሰብ የሚሹ አካላት ከሚመለከተው ክፍል ፈቃድ በመጠየቅ ስብሰባ ማካሄድ መጀመራቸውን ነው ዶክተር ሊያ የተናገሩት።

መመሪያውን በመከተል እየተከናወኑ ያሉ የጥንቃቄ ተግባራት አበረታች ቢሆኑም በሽታውን ለመቆጣጠር ከሚጠበቀው አንጻር ግን "ብዙ ይቀራል" ብለዋል።

መመሪያውን በመጣስ ርቀት ያልጠበቁ፣ ከተፈቀደው ቁጥር በላይ የሰዎች ስብስብ የያዙና ያለማስክ የተደረጉ ስብሰባዎችና የድጋፍ ሰልፎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫና በሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ጥግግት ተስተውሏል ነው ያሉት።

በዚህም የበሽታው ስርጭት ምጣኔ እየጨመረ መሆኑንና እስካለፈው ቅዳሜ በነበሩ 10 ተከታታይ ቀናት ከ20 ሺህ 600 ሰዎች በላይ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው አንስተዋል።

ይህ አሃዝ ከአንድ ወር በፊት በነበሩ 10 ቀናት በቫይረሱ ተይዘው ከነበሩት ሰዎች ጋር ሲነጻጸር የ91 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው የተናገሩት።

እስከ ትናንትና ድረስ የጽኑ ሕክምና የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና ባለፉት 10 ቀናት ብቻ በህክምና ተቋማት ውስጥ 275 ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን ገልፀዋል።

ይህም በአሁናዊው መረጃ መሰረት በቀን እስከ 28 ሰዎች በኮቪድ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ አመላካች ነው ብለዋል።

በመሆኑም በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት በዓርአያነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዶክተር ሊያ ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ተቋማትን አቅም ለመገንባት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም አገሪቷ ያላት ሃብት ውስን በመሆኑ ኅብረተሰቡ ሳይዘናጋ ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው መጋቢት በመዲናዋ የመቃብር ስፍራዎች ባካሄደው ጥናት የሞት መጠኑ ከአምና ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ37 በመቶ ጭማሪ እንዳለው አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም