በመተከል ዞን በሁሉም ወረዳዎች መደበኛ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ነው

77

ሚያዚያ 8 /2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተዋቀረው ኮማንድ ፖስት በአካባቢው አስተማማኝ ሠላም ለማስፈን በሰራቸው ስራዎች በሁሉም ወረዳዎች መደበኛ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለፀ።

በመከላከያ ሠራዊት መሪነት የተዋቀረው ኮማንድ ፖስቱ ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት መውደምን ማስቆምና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደህንነትን የመጠበቅ ተልእኮውን እየተወጣ መሆኑም ተነግሯል።

የመከላከያ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሰጡት መግለጫ በአካባቢው የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ ክንውኖች፤ የባንክና የትራንስፖርት እንዲሁም የሰፋፊ እርሻ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

ከከተማ ወደ ጫካ የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ስራ መሰራቱንና ከዞኑ ተፈናቃዮችም ጋር ሕዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸውን ገልፀዋል።

በዞኑ ታጣቂዎችን ወደ ሠላም የመመለስ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውንና በቀጣይም ኮማንድ ፖስቱ አስተማማኝ ሠላም እንዲረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን ኮሎኔል ጌትነት ተናግረዋል።

የሕዳሴ ግድብን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለግድቡ ግንባታ የሚጓጓዙ ግብዓቶችን የማጀብ ስራዎችና ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

"የአካባቢውን ሠላም ወደ ነበረበት ለመመለስ እየተሰራ ባለበት የአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያውን የጨለመ አስመስለው መመልከት ተገቢ አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።

በአካባቢው ምንም እንዳልተሰራና ሠላም እንደሌለ ሀሰተኛ መረጃና ውዥንብር የሚፈጥሩ የማህበራዊ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች እንዳሉ ጠቁመው፤ ሕዝቡ ከሀሰተኛ መረጃዎች ራሱን እንዲጠብቅ አስገንዝበዋል።

አብን የምክር ቤት ዕጩዬ "ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ ሲሄድ ከመኪና እንዲወርድ ተደርጎ ተገደለ" በሚል ስላሰራጨው መረጃና በግልገል በለስ ከተማ ስለተገደሉት የሆቴል ባለቤት በተመለከተም በሰጡት ማብራሪያ ግለሰቦቹ ህይወታቸውን ያጡት በግጭት ውስጥ በመሳተፋቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ጉዳዩን ማጣራት የሚፈልግ ማንኛውም አካል በስፍራው ተገኝቶ ማጣራት እንደሚችልም ገልጸዋል።

መከላከያ በፖለቲካ ፓርቲዎች ርዕዮተ ዓለም ጣልቃ እንደማይገባ ሁሉ ፖለቲከኞች የራሱ ሙያና አሰራር ባለው ኢትዮጵያዊ ሠራዊት ጉዳይ መግባት አይገባቸውም ሲሉም ኮሎኔሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም