በኢትዮጵያ ከ430 ሺህ በላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት ተከትበዋል - ጤና ሚኒስቴር

76

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8 /2013 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) መከላከያ ክትባት መሰጠት ከጀመረበት ካለፈው መጋቢት 4 ቀን ጀምሮ እስካሁን ከ430 ሺህ በላይ ሰዎች መከተባቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የወረርሽኙን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም የኮቪድ-19 ክትባት መሰጠት ከጀመረበት እስከ አሁን ድረስ ከ430 ሺህ በላይ ዜጎች መከተባቸውን ገልፀዋል።

ክትባቱን የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች፣ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ የጤና እክል ኖሮባቸው ዕድሜያቸው ከ55 እስከ 64 የሆኑ ዜጎች ክትባቱን እየወሰዱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ክትባቱ ከሌሎች የክትባት አይነቶች በተለየ መልኩ ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን የገለጹት ዶክተር ሊያ፤ ከተለያዩ አገራት የሚወጡ መረጃዎችና በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በየጊዜው የሚገመግም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

በቅርቡ ተጨማሪ ክትባት ለማስገባት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ነው ዶክተር ሊያ የገለጹት።

በሁሉም ክልሎች የክትባት መስፈርቱን የሚያሟሉ፣ በዕድሜያቸው የገፉና ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው እንዲሁም ተፈናቃዮችና ስደተኞች ባሉባቸው ካምፖች ጭምር ክትባቱ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ስለ ክትባቱ የሚነገሩ የተሳሳቱ መረጃዎች ሳይበግራቸው ክትባቱን እየወሰዱ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች፣ እናቶችና አባቶች ዓርአያ በመሆናቸው ምስጋና እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል።

ለሕዝበ ሙስሊሙ የእንኳን ለጾም ወር አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ዶክተር ሊያ፤ የእምነቱ ተከታዮች በአምልኮ ስነ-ስርዓት ወቅት አካላዊ ርቀት በመጠበቅ፣ ማኅበራዊ ስብስብን በመቀነስና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በመጠቀም የረመዳንን ወር በጥንቃቄ እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም