ዩኒቨርሲቲዎች በትኩረት መስክ መለየት የምርምር ውጤቶቻቸው ችግር እንዲፈቱ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ምሁራን ገለጹ

93

ዲላ ሚያዚያ 8/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በትኩረት መስክ መለየታቸው የምርምር ውጤቶቻቸው ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር የከፍትኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ገለጹ።

"ምርምር ለማህበረሰብ ለውጥ" በሚል መሪ ሀሳብ  ለሁለት ቀናት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ የቆየው አስረኛው ሀገር አቀፍ የምርምርና ጥናት ኮንፍረስ ትናንት  ማምሻውን   ተጠናቋል።

ከኮንፊረሱ ተሳታፊዎች መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተባረክ ኢክራም በሰጡት አስተያየት የበለጸጉት ሀገራት  ልማትን በማረጋገጥ የማህበረሰባቸውን መሰረታዊ ችግርን ማቃለል የቻሉት በእውቀት  ላይ የተመሰረተ ምርምር ተግባራዊ በማድርጋቸው ነው።

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ  ለሚስተዋሉ መጠነ ሰፊ ችግሮች መፍትሄ መስጠት የሚቻለው በምርምርና ጥናት መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ነገን ታሳቢ ያደረጉ ማህበረሰብ አቀፍ ምርምሮች በስፋት ሊከናወኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ አንፃር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትኩረት መስክ መለየታቸው በተበታተነ መንገድ የሚሰሩ ጥናቶችን ወደ አንድ ቋት ከመሰብሰብ ባለፈ የምርምር ውጤቶች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

በተለይ ምርምሮች ከተለያዩ ተፅዕኖዎች ነፃ ከመሆን ባለፈ ተጠቃሚውን ማህበረሰብ አሳታፊ ማድረግ ከቻሉ ለውጥ መምጣት  እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሳምሶን ሃይለማሪያም በበኩላቸው፤  ምርምሮች በሚፈለገው መጠን የማህበረሰቡን ችግሮች እንዲያቃልሉ ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ማድግ እንዳለበት ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትኩረት መስክ መደራጀታቸው ከአሁን በፊት እንደ ድክመት ሲነሳ የነበረውን የምርምር ውጤቶች ከሼልፍ ላይ ተነስተው ለማህበረሰቡ ችግሮች ተጨባጭ ምላሽ እንዲሰጡ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በዲላ  ዩኒቨርሲቲው የሚያወጣቸው የምርምር ውጤቶች ማህበረሰቡ ጋር እንዲደርሱ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬሕይወት እንዳለ ናቸው።

ሆኖም የጥናት ጽሁፎች ለሀገሪቱ አንገብጋብ አጀንዳዎችና እድገት ምላሽ ከመስጠት አንጻር ውስንነቶች እንዳሉባቸው ገልጸዋል።

ሆኖም ሌሎችንም በምርምር መስኩ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው የምርምር የትኩረት መስኮችን በመለየት አበክሮ በመስራት  ላይ እንደሚገኝ    አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲተው በትኩረት  መስክ መለየቱን ተከትሎ በግብርና፣ ጤና፣ ትምህርትና ኢኮ ቱሪዝም የትኩረት መስኮች ተግባር ተኮር ምርምሮችን በማከናወን ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት እየተጋ መሆኑን አስረድተዋል።

በኮንፍረንሱ ከሀገር ውስጥና ውጭ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተጋበዙ ተመራማሪዎች፣  የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሃላፊዎች እንዲሁም የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም