በረመዳን ፆም ወቅት የእምነቱ ተከታዮች በመረዳዳትና አብሮነት ሊያሳልፉ እንደሚገባ የእምነቱ አባቶት ተናገሩ

79

ሀዋሳ፣ ሚያዝያ 08/2013(ኢዜአ) በረመዳን ፆም ወቅት የእምነቱ ተከታዮች ከሌላው ጊዜ በተለየ መልክ ማህበራዊ እሴቶችን በማጠናከር ለሀገር ሠላምና አብሮነት ሊያሳልፉት እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የእምነቱ አባቶች ተናገሩ።

በደቡብ ክልል የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ዋና ቃዲ ሼህ አብራር ሺፋ እንዳሉት፤ ረመዳን ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ታላቅና የተቀደሰ ወር ነው፤ በቀልቡም፣ በምግባሩም ከፈጣሪ ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ የሚተጋበት ነው።

መተዛዘንና መረዳዳት አንዱ ለሌላው ያለውን ሠላማዊ የሆነ ዕይታ በጉልህ የሚያሳይ እንደሆነ ጠቅሰው   ሙስሊሞች ከቤተሰቦቻቸው አልፈው በእምነት እንኳ ከማይመስሏቸው ጎረቤቶቻቸው ጋር ጭምር ያላቸውን ተካፍለው እንዲኖሩ የኢስላም አስተምህሮት እንደሚያዝ ገልጸዋል።

ይህ መልካምነት የተሞላበት የእርበእርስ ግንኙነት ደግሞ እንደ ሀገር ሠላምና አብሮነትን ለመገንባት የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ከአላህ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማጥበቅ ስብዕናችንን የምንገነባበት የሥልጠና ወር ነው ብለዋል።

በረመዳን ፆም ሁሉም ስለ ኢትዮጵያ መፀለይ እንዳለበት ጠቁመው በተለይ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚስተዋሉ አስከፊ ነገሮች ሁሉ እንዲወገዱ መፀፀትና ንስሀ መግባት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በሀዋሳ  የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መስጂድ ኢማም   ሼህ ኡመር ቡሽራ በበኩላቸው፤ ረመዳን እጃችንን ለበጎ ምግባር የምንዘረጋበትና ይቅር የምንባባልበት ወር ነው ብለዋል።

ይህ ምግባር ለሠላም ያለው አበርክቶ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን አመልክተው  ሁሌም መተግበር እንዳለበት ተናግረዋል።

"ሠላም ከአላህ በፀጋ የተሰጠን ነገር ግን ካጣነው ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለን ነው" ያሉት ሼህ ኡመር ይህን የፈጣሪ ፀጋ በአግባቡ ለመጠቀም በፆም ወቅትም ሆነ ከፆም ውጭ ከሁሉም ጋር ሠላማዊ ግንኙነት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች ደማቸው በከንቱ የሚፈስ የማንኛውም እምነት ተከታዮች ወገኖቻችን በመሆናቸው ስለ እነርሱ ማሰብ ግድ ይለናል ብለዋል።

 እርስ በእርስ የሚያጋድሉ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዚሁ መስጂድ ካዲም የሆኑት ሀጂ ቃሲም ጉዬ በበኩላቸው የሰው ልጅ እርስ በርሱ ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋርም ተስማምቶ መኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ረመዳን  ይቅርታና ምህረት ወር በመሆኑ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሁሉም ጋር በሠላም ለመኖር መጣር እንዳለበት  ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም