የጎርጎራ ከተማ የ20 ዓመት መዋቅራዊ ፕላን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተዘጋጀ ነው

91

ጎንደር፤ ሚያዚያ 8/2013 (ኢዜአ) በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የታቀፈቸውን የጎርጎራ ከተማ  ለ20 አመታት የሚያገለግል መዋቅራዊ ፕላን እያዘጋጀ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።


ዩኒቨርሲቲው በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት ላይ ግብአት ለማሰባሰብ የሚያስችለውን ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ እያካሄደ ይገኛል። 

በዩኒቨርሲቲው የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል መምህርና የመዋቅራዊ ፕላኑ ዝግጅት አስተባባሪ አቶ አየልኝ ተበጀ እንደተናገሩት መዋቅራዊ ፕላኑ የከተማዋን የወደፊት እድገትና የኢንቨስትመንት ፍሰት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

“ጎርጎራ በገበታ ለሀገር ከታቀፈችበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የኢንቨስትመንት ፍሰት ወደ ከተማዋ እየመጣ ነው” ያሉት አቶ አየልኝ ፍሰቱን በአግባቡና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመምራት መዋቅራዊ ፕላኑ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።

ጎርጎራ በርካታ ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባህላዊ እሴቶችን ያቀፈች ከተማ እንደመሆኗ መዋቅራዊ ፕላኑ ይህን  እሴት በጠበቀ መንገድ የወደፊት ልማቷን ታሳቢ አድርጎ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አራት ወራት ለመዋቅራዊ ፕላኑ ዝግጅት በግብአትነት የሚውሉ መረጃዎችን በማሰባሰብና በማደራጀት ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሲሰራ መቆየቱንም ገልጸዋል።

“መዋቅራዊ ፕላኑ በየደረጃው በህዝብ እንዲተች በማድረግና በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ በቀጣዩ አመት ወደ ትግበራ የሚገባባት ሁኔታ ይመቻቻል” ብለዋል፡፡ 

በመዋቅራዊ ፕላን ዝግጅቱ ላይ በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ 14 የትምህርት ክፍሎች የተውጣጡ ከ30 በላይ ባለሙያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡ 

የጎርጎራ ከተማ እምቅ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ሀብቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በምርምር ለማገዝ መታቀዱን የገለጹት የዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ቢኒያም ጫቅሉ ናቸው፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው “የክልሉ መንግስት የጎርጎራ ከተማን መዋቅራዊ ፕላን ዩኒቨርሲቲው እንዲያዘጋጅ ሃላፊነት ከሰጠበት እለት አንስቶ የተለያዩ ከሚቴዎችን አዋቅሮ እየሰራ ነው” ብለዋል፡፡

ጎርጎራ የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ መዋቅራዊ ፕላኑ ተጠናቆ ለፍጻሜ እንዲበቃ ዩኒቨርሲቲው ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ 

ዩኒቨርሲቲው ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው መድረክ ላይ በከተሞች ፕላን ዝግጅት ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ 

ተሞክሮዎችን የዳሰሱ ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን የሚቀርቡ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የባህልና ቱሪዝም የስራ ሃላፊዎች ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም የህዝብ ወኪሎችም ታዳሚ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም