ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ለመራጭነት የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ ከወዲሁ እንዲወስድ ጥሪ ቀረበ

52

ባህርዳር ኢዜአ ሚያዚያ 8/2013 በመጪው ግንቦት ወር ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በአማራ ክልል ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ለመራጭነት የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ ከወዲሁ ተመዝግቦ እንዲወስድ ጥሪ ቀረበ።

በክልሉ  በ138 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 12 ሺህ 199 ምርጫ ጣቢያዎች መቋቋማቸውን  በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መኳንንት መከተ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የምርጫ ቁሳቁስ ፈጥኖ መድረስ ባለመቻሉ የመራጮች ምዝገባ 15 ቀናትን ዘግይቶ  ነው የተጀመረው።

እስካሁንም የተሟላ የመራጮች ምዝገባ የተጀመረው  ከተቋቋሙት ውስጥ በ131 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 11 ሺህ 357 ጣቢያዎች እንደሆነ ተናግረዋል።

በቀሪዎቹ  በተለያየ ወቅታዊ ችግር ምክንያት እስካሁን እንዳልተጀመረ ገልጸዋል።

የመራጮች ምዝገ ዘግይቶ ከመጀመሩም ባለፈ አሁንም ድረስ ለምርጫ የሚያበቃውን ካርድ ተመዝግቦ በመውሰድ በኩል የህብረተሰቡ እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም በክልሉ ለመራጭነት ይመዘገባል ተብሎ ከሚጠበቀው 10 ሚሊዮን ህዝብ እስካሁን ተመዝግቦ የምርጫ ካርድ መውሰድ የቻለው 15 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

የመራጮች ምዝገባ የሚያበቃው ሚያዚያ 15/2013 መሆኑን በመገንዝብ ህብረተሰቡ  ሳይዘናጋ ለመራጭነት የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ ተመዝግቦ እንዲወስድ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ጥሪ አቅርበዋል።

በባህር ዳር ከተማ ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ጋሻው መለሰ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት የተካሄዱ አምስቱንም ምርጫዎች በመራጭነትና በአስመራጭነት መሳተፋቸውን  ተናግረዋል።

''ዛሬ ለመራጭነት የሚያበቃኝን የምርጫ ካርድ ተመዝግቤ የወሰድኩት በስድስተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ይመራኛል፣ ያስተዳድረኛል ብየ ያመንኩበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለይቼ ለመምረጥ ነው'' ብለዋል።

በዘንድሮው  የመራጮች ምዝግባ  መቀዛቀዝ የታየበት ነው ያሉት አቶ ጋሻው  ህብረተሰቡ ለመራጭነት የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ ተመዝግቦ እንዲወስድም የተጠናከረ ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አካል ጉዳተኛ  አቶ ገብረስላሴ  ሞገስ በበኩላቸው  ለአካል ጉዳተኞችና  ለሀገሪቱ የሚጠቅም ፕሮግራም ይዞ የሚቀርበውን የፖለቲካ ፓርቲ  ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ተመዝግበው መውሰዳቸውን  ገልጸዋል። 

''ይወክለኛል የምለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችለኝን ካርድ እንደወሰድኩ ሁሉ ሌላውም ወጣት የሚሆነውን ለመምረጥ ከወዲሁ ተመዝግቦ የምርጫ ካርድ ሊወስድ ይገባል'' ያለው ደግሞ ወጣት ፍቅሬ ቢረሳው  ነው።

ከዚህ በፊት እንደነበሩት ምርጫዎች ምዝገባው ያልተሟሟቀው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጨመር ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችልም አስተያየቱን ሰጥቷል።

በመራጩ ህዝብ ዘንድ እየተስተዋለ ያለውን መዘናጋት ለማስቀረት ጠንካራና የተደራጀ ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁሟል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ  ግንቦት 28/2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ  ብሄራዊ  ምርጫ  ቦርድ ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም