ከነገ ጀምሮ ለ7 ቀናት የሚዘልቅ አገር አቀፍ ጸሎትና ምህላ ይከናወናል

71

ሚያዚያ 07 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከነገ ጀምሮ ለ7 ቀናት የሚቆየውን የጸሎትና የምህላ መርሃ ግብር ከሁሉም ቤተ እምነቶች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ዛሬ በእወጃ አስጀምረዋል።

ጸሎትና ምህላው በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን በማስጀመሪያ መርሃ ገብሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተገኝተዋል።

ከተለያዩ ቤተ እምነቶች የተወከሉ የሃይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ታድመዋል።

ጸሎትና ምህላው ያስፈለገው በአገሪቷ የሚስተዋለው የሠላምና መረጋጋት እጦት፣ የዜጎች መፈናቀልና ሞት እንዲቆም በአንድነት ለመቆም ነው።

ዘርና ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እንዲቆሙ፣ መጪው አገራዊ ምርጫ በሠላም እንዲከናወንና እየተባባሰ የመጣው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እልባት እንዲያገኝ በአንድነት መጸለይ ስለሚገባ እንደሆነም ተገልጿል።

በፀሎትና ምህላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ከሰባት የሃይማኖት ተቋማት የመጡ አባቶች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በጋራ የጸናች ኢትዮጵያን ወደ ሠላሟ ለመመለስ በጋራ መፀለይ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜንና ደቡብ ወሎ አህጉረ ስብከትና በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤርሚያስ ቤተክርስቲያ ለአገር ስትጸልይ መኖሯን ገልፀዋል።

ከነገ ጀምሮ ለሰባት ቀናት በሚከወነው አገራዊ ጸሎትና ምህላ በተለይ የአገር መሪዎች ስለ አገራቸው እንዲጸልዩም ጥሪ አቅርበዋል።የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ሼኽ ሃሰን መሀመድም የጋራ የሆነች አገር ኢትዮጵያን ተስፋ ለማለምለም በጋራ ልንጸልይ ይገባል ሲሉ መለዐክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁህ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው የበደለ በጸሎትና በመጸጸት ንሰሃ እንዲገባ አሳስበዋል።

የሃይማኖት አባቶችም በአገልግሎት ደክመን ከሆነ እግዚሃብሄርን ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባል ብለዋል።የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶም ሕዝቡ በአንድ ልብ ሊጸልይ ይገባል ብለዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት፣ ወንጌላዊት መካነ እየሱስ እና ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያናት አባቶችም የፀሎትና ምህላ መልዕክትና አዋጃቸውን አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጸሎትና ምህላው አገሪቷ ላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ትልቅ ፋይዳ አለው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም መላው ኢትዮጵያዊያን በጸሎትና ምህላው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከነገ ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚዘልቀው ፀሎትና ምህላ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በሁሉም የሕዝብና የግል ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎች ከምሽቱ 3 ሠዓት እስከ 4 ሠዓት በቀጥታ የሚተላለፍ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም