ኅብረተሰቡ ጤናን ከሚጎዱ ሕገወጥ የምግብና የመድኃኒት ምርቶች ሊጠነቀቅ ይገባል....ባለስልጣኑ

60

ሚያዚያ 7/2013(ኢዜአ) ኅብረተሰቡ የጤና እክል ሊያደርሱ ከሚችሉ ሕገወጥ የምግብና የመድኃኒት ምርቶች እንዲጠነቀቅ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አሳሰበ።

ባለስልጣኑ ኅብረተሰቡ ጤናውን ከሚጎዱ ሕገወጥ የምግብና የመድኃኒት ምርቶች እንዲጠነቀቅ የማስገንዝብ ንቅናቄ እያካሄደ ነው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በአገሪቷ ሕገወጥ የምግብና የመድኃኒት ንግድ እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።

ሕግወጥ ተግባሩን ለመከላከልና ኅብረተሰቡም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ለማስቻል በአርባ ምንጭ፣ በጅማ፣ በደሴና ጂግጂጋ ከተሞች የሕዝብ ንቅናቄ መድረኮች መካሄዳቸውንና በአዲስ አበባ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

መድረኮቹ ከምግብና መድኃኒት ጥራትና ደህንነት ጋር በተያያዘ  ካልተገባ የመድኃኒት አጠቃቀም፣ ከሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውር፣ የትምባሆና አደንዛዥ ዕጽ ችግሮችን ለኅብረተሰቡ ለማስገንዘብ ያለሙ ናቸው።

ጉዳዩን ለኅብረተሰቡና ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ የቁጥጥር ሥራው አካል እንዲሆኑ የማድረግ ግብ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

መድረኮቹ ሕገወጥ ተግባራቱን በመከላከሉ ሥራ ኀብረተሰቡ የራሱን አስተዋፅኦ በማድረግ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ያግዛሉም ነው ያሉት።

ንቅናቄው በጎዳና ላይ ቅስቀሳ፣ የተለያዩ መልዕክቶችን የያዘ ቢልቦርድ በመስቀል፣ ብሮሸሮች፣ ሲዲዎችና ባነሮችን ለተለያዩ አካላት በማሰራጨት እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

የባለስልጣኑ የምግብ ኢኒስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ጋሻው አለማየው የዓለም የጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የግብርና ድርጅት እ.እ.አ በ2020 ባወጡት መረጃ በዓለም ላይ በየዓመቱ 600 ሚሊዮን ሰዎች በተበከለ ምግብ ሳቢያ ለሕመም ይዳረጋሉ፡፡

420 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በዚሁ ችግር ምክንያት ሕይወታቸው ያልፋል።

እንደ አቶ ጋሻው ገለጻ በኢትዮጵያም በተበከሉ ምርቶች ሳቢያ በርካቶች ለጤና ችግር እየተጋለጡ ነው።

አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጥራትና ደረጃ የማያሟሉ፣ ደህንነታቸው ያልተጠበቀ፣ በአግባቡ ያልተመረቱ፣ ያልተጓጓዙና ያልተከማቹ፣ ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸውና ገላጭ ፅሁፍ በአግባቡ ያልተቀመጠባቸው ምርቶች ለኅብረተሰቡ እንደሚሰራጩም ጠቁመዋል።

ለዚህም የግንዛቤ እጥረት፣ በቁጥጥር ስራው ላይ የነቃ ተሳትፎ ያለማድረግ፣ የህግ ጥሰቶች ተፈፅመው ሲገኙ ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል ያለማሳወቅ ክፍተቶች መኖር ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም ጥራታቸው፣ ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ባልተረጋገጡ ምርቶች ሳቢያ ሕብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችልን የጤና ጉዳት ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጻል ነው የተባለው።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የሕዝብ ንቅናቄ መድረክ በመጪው እሁድ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም