የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የተጀመረውንየዲጂታል ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ...ዶክተር አብርሃም በላይ

62

ሚያዚያ 7 / 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በቅርቡ የተጀመረው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ፡፡

የአማርኛ፣ አፋር ኦሮሞ፣ ሱማሌኛና ትግርኛ ቋንቋዎች ማሽኖችን በማስተማርና በማሰልጠን በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አጥኝዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ስራ እንደተጀመረም ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውና ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆየው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዓውደ ጥናትና ዓውደ ርዕይ "አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሁሉም" በሚል መሪ ቃል ዛሬ ተጀምሯል፡፡

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 463/2012 መንግሥታዊ መስሪያ ቤት ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን መስከረም 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተመርቆ በይፋ ስራ መጀመሩ ይታወቃል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰው ልጅ በተፈጥሮና በህይወት ዑደት የሚያገኛቸውን የማሰብ፣ መገንዘብ፣ ማመዛዘን፣ ማቀድ፣ ምክንያታዊ የመሆን፣ የመማርና በቋንቋ የመግባባት ክህሎትን በረቀቀ ቀመር ማሽኖችን በማስተማር የተለያዩ አይነት ተግባራትን ማከናወን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂና ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ ፋይናንስ፣ ትራንስፖርት ሚቲዎሮሎጂ፣ ኤሮስፔስ እና ሌሎች ዘርፎች ገቢራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡

ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ አካታች ብልጽግና ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

"የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል" እንዲሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል በተቋቋመ በጥቂት ወራት ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ከጅምሩ አሳይቶናል ነው ያሉት፡፡

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና የሰው ሰራሽ አስተውሎት በረቀቀ ቀመር ማሽኖችን በማስተማርና በማሰልጠን ለዜጎች ችግር መፍትሄ የሚያፈላልግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ማዕከሉ አራት ቋንቋዎችን በመለየትና የዳታ ክምችት ስርዓቱን በማዘመን ዓለም አቀፍ የጥናትና መርምር ተቋማት ስለ ኢትዮጵያ በቂ ጥናት እንዲያደርጉ ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ስለ አማርኛ፣ አፋር ኦሮሞ፣ ሱማሌኛና ትግርኛ ቋንቋዎች ማሽኖችን በማስተማርና በማሰልጠን ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ማዕከሉ ሀገር አቀፍ ምርምርና ልማት ማዕከል በማቋቋም የመለኪያ መስፈርቶችን በማዘጋጀት የዲጂታል ዳታ ክምችትን በጥራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና።

በግብርና፣ ጤና፣ ትራንስፖርት በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ወደ ምርት ደረጃ የተሸጋገሩ በምስለ ምርት ደረጃ እና በሙከራ ላይ ያሉ ስራዎች በማዕከሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በቅልጥፍና መስራት የሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ ነን ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያደረጋቸው ውይይቶችና ስምምነቶች ለሌሎች ተቋማትም አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ለቴክኖሎጂው ስርጸትና መስፋፋት ከማዕከሉ ጋር የሚያደርገው ቅንጅታዊ አሰራር ቀጣይነት ይኖረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም