በመዲናዋ የድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች ውል ለሁለት ወራት ተራዘመ

105

ሚያዚያ 7/2021 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች ውል ለሁለት ወራት መራዘሙ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ስጦታው አካለ የመዲናዋን የትራንስፖርት አሰጣጥ  አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመዲናዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ቢሮው በወሰደው የመፍትሔ ሃሳብ ከስድስት ወር በፊት ድጋፊ ሰጪ አገር አቋራጭ አውቶብሶች በኪራይ ወደ ስምሪት መግባታቸውን አስታውሰዋል።

እነዚህ አውቶቡሶች ወደ ስምሪት ከገቡ ጊዜ አንስቶ የአገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል።

አቶ ስጦታው በከተማዋ የትራንስፖርት ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር ተያይዞ ባለመጣጣሙ ረዣዥም ሰልፎች እንደሚታይ እና ከ45 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት የትራንስፖርት ጥበቃ የቆይታ ጊዜ እንደነበር አንስተዋል።

ድጋፊ ሰጪ አውቶቡሶችን ወደ ስምሪት ከገቡ ወዲህ የቆይታ ጊዜ በአማካይ ወደ 12 ደቂቃ ዝቅ ማድረግ መቻሉን እና ሲሰተዋል የነበረው ሰልፍም መቃለል መቻሉን ቢሮ ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን ተናግረዋል።

ሌሎች የብዙሃን ትራንስፖርት ሰጪዎች የማይደርሱባቸው ቦታ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም አክለዋል።

በመግለጫው አስተዳደሩ ከድጋፊ ሰጪ አውቶብሶች ጋር የነበረው ውል ለስድሰት ወራት እንደነበር እና ውል መጠናቀቁን ገልፀዋል።

አውቶቡሶቹ በመዲናዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር በማቃለልና በሰፊው ለውጥ ማምጣቸው ከግንዛቤ በማስገባት በአስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ መሰረት ለቀጣይ ሁለት ወራት እንዲቀጥሉ ውሉ መራዘሙን ገልፀዋል።

ከወቅታዊ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ለአውቶቡሶች በውሉ መሰረት የኪራይ  የዋጋ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረው ማሻሻያውን ተከትሎ በተጠቃሚዎች ላይ የታሪፍ ማሻሻያ እንደማይደረግ አረጋግጠዋል።

ድጋፊ ሰጪ አውቶብሶቹ በቁጥር 350 እንደሆኑ አንስተው ሁሉም አውቶቡሶች ላይ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ተገጥሞላቸው በሰሩት ልክ ክፍያ እየተፈፀመ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም