የአዲስ አበባ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች ለ2 አገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ አደረጉ

108

ሚያዚያ 7/2021 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች ለ'የወደቁትን አንሱ' እና ለ'ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን መርጃ' ከ650 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

አመራሮቹ ዜጎችን ከጎዳና ለማንሳት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ጠይቋል፡፡ 

ለሁለቱ ተቋማት የተበረከተው ድጋፍ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ፣ አንሶላ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ አልኮልና ሳኒታዘር አካቷል፡፡ 

ድጋፉን ለድርጅቶቹ ያስረከቡት የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ እጅጉ አመራሮቹ ያደረጉት ድጋፍ ሕዝባዊነትና አብሮነትን ያመላክታል ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በጎ ተግባር ለሚያከናውኑ ድርጅቶች የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክርም ቃል ገብተዋል፡፡

ዜጎች በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በቀና አስተሳሰብ በመነሳሳት እንዲደግፉም ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ማሞ የተቋማቱ አመራሮች የራሳቸውንና ሌሎችንም በማስተባበር ያደረጉት ድጋፍ በአርዓያነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል፡፡

የወደቁትን አንሱ የነዳያን ማኅበር መስራች አቶ ስንታየሁ ተበጀ በበኩላቸው ማኅበራቸው ከጎዳና ላይ የተነሱ 350 ነዳያንን በመንከባከብ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው አመራሮቹ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

የጌርጌሴኖን አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር መስራች አቶ መለሰ ሲሳይም 450 ተረጂዎችን ለሚያስተናግደው ድርጅታቸው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዜጎችን ከጎዳና በማንሳት በመርዳት ተግባር የተሰማሩ 64 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንደሚገኙ ማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም