የጢያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጥገና ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ

112

ሚያዚያ 7/2013 (ኢዜአ) የጢያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጥገና ተጠናቆለት ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ።

ለመካነ ቅርሱ ጥገና ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተገልጿል።

ጥገናውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋራ አከናውነውታል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ የመካነ ቅርሱ ጥገና ቅርሱ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ከማስቻሉ ባለፈ ለአካባቢው ልማት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የጥገና ስራው ባለፈው ዓመት ቢጀመርም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ መደረጉን አስታውሰዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የመካነ ቅርሱ ጥገና ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ መፍጀቱንም ነው የገለጹት።

የጥገና ስራው ወደ አንድ አቅጣጫ ያጋደሉ ድንጋዮችን የማቅናት፣ የሳር ምንጠራና ቦታውን የመደልደል እንዲሁም አሲዳማ አፈሩን ማከምን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በቅርሱ አካባቢ የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም የተለያዩ ስራዎችን በፍጥነት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተለይ በጅማሮ ላይ ያለውን የባሕል ማዕከል ግንባታ ማፋጠንና የመዝናኛ ስፍራዎችን ማስፋፋት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የአካባቢው ባለሃብቶችና መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለጢያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ የተደረገው ጥገና የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን በቀጣይ መሬቱን ሳር የማልበስና ተያያዥ ስራዎች እንደሚቀሩ ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል።

ለቀሪዎቹ ስራዎች የአካባቢው ማኅበረሰብ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የጢያ ትክል ድንጋዮች ከ12ኛው እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መተከላቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በመካነ ቅርሱ ቅጥር ግቢ 41 የቁም ትክል ድንጋዮች የሚገኙ ሲሆን የአንዳንዶቹ ድንጋዮች ቁመት እስከ አምስት ሜትር ይደርሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም