በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ314 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገ

73

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 07 / 2013( ኢዜአ)  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ314 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የይቅርታ ቦርድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ስሜነህ ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ይቅርታ ከተደረገላቸው   የህግ ታራሚዎች መካከል ሰባቱ ሴቶች ናቸው፡፡

ይቅርታውን ያገኙት የህግ ታራሚዎች በክልሉ አሶሳ፣ ካማሽ እና መተከል ዞኖች ማረሚያ ቤቶች የነበሩ  የህግ ታራሚዎች እንደሆኑ አመልክተዋል።

በክልሉ ይቅርታ ቦርድ ተገምግመው ይቅርታ ያገኙት ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በፈጸሙት ወንጀል የተጸጸቱ፣ የታረሙ እና በተሰጣቸው ስልጠና የታነጹ መሆናቸውን የገለጹት  አቶ ስሜነህ ከህብረተቡ ቢቀላቀሉ አምራች ዜጋ እንደሚሆኑ ታምኖ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ታራሚዎቹ በቀላል ስርቆት፣ ማጭበርበር፣ በእለታዊ አጋጣሚ በተከሰተ ግጭት ምክንያትና ሌሎች  ወንጀሎችን ፈጽመው በፍርድ ቤት ከተጣለባቸው የእስር ቅጣት ከአንድ ሶስተኛ በላይ ጊዜ ያጠናቀቁ ናቸው ብለዋል፡፡

ይቅርታው በሃገሪቱ ህግ መሠረት ይቅርታ የማያሰጡ ውንብድና፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጠለፋ፣ ከባድ የሰው ግድያ እና ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን የፈጸሙ ታራሚዎችን እንዳላካተተ  ገልጸዋል፡፡

ይቅርታው መስጠት የተጀመረው ከሚያዚያ 06 / 2013 ዓ.ም አንስቶ  እንደሆነ አቶ ስሜነህ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም