የጥያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጥገና ተደርጎለት ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ

461

ሚያዚያ 7/2013 (ኢዜአ) የጥያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጥገና ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ።

ለመካነ ቅርሱ ጥገና ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተገልጿል።

የመካነ ቅርሱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጥገና ተጠናቆ ዛሬ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል።


ከአዲስ አበባ በ82 ኪሎ ሜትር ርቀት በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ የሚገኘውን የጥያ ትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ በ1972 ዓ.ም ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል።

የጥገና ስራው ወደ አንድ አቅጣጫ ያጋደሉ ድንጋዮችን የማቅናት፣ የሳር ምንጠራና ቦታውን የመደልደል እንዲሁም አፈሩን ማከምን ያጠቃለለ ነው።

ጥገናውን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዳከናወነው ተገልጿል።

የጥያ ትክል ድንጋዮች ከ12ኛው እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መተከላቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በመካነ ቅርሱ ቅጥር ግቢ 41 የቁም ትክል ድንጋዮች የሚገኙ ሲሆን የአንዳንዶቹ ድንጋዮች ቁመት እስከ አምስት ሜትር ይደርሳል።

መካነ ቅርሱ ለጎብኚዎች በተከፈተበት መርሃ ግብር የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ፣ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳደር የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም