ሰው በማገት ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

86

መተማ ፤ ሚያዚያ 7/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በማስቆም አምስት ሰዎችን በማገት ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የወረዳው ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ መላኩ ሲሳይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ምህረት ወርቁ የተባለው ግለሰብ ታህሳስ 15/ 2012 ዓ.ም በወረዳው ቁጥር አራት  ቀበሌ በመነሳት ወደ ጎንደር ይጓዝ የነበረን የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በማስቆም ሰዎችን የማገት ወንጀል ፈጽሟል።

ለጊዜው ካልተያዙ ዘጠኝ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን አምስት ተሳፋሪዎችን አግተው በማቆየት ከማሰቃየታቸውም ባለፈ  620 ሺህ ብር አስከፍለው መልቀቃቸውን በቀረበ ማስረጃ መረጋገጡን ገልጸዋል።

ወንጀሉን ከፈፀሙ በኋላም በአካባቢው በመሰወራቸው ፖሊስ ለመያዝ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ከመካከላቸው ግለሰቡ ጥር 23/2013 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውሎ ክስ እንደተመሰረተበት ባለሙያው አስረድተዋል።

ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈፀመ በኋላ ከህግ ተሰውሮ ሌሎች ተደጋጋሚ ወንጀሎችን ሲፈፅም መቆየቱን በሰውና ሰነድ ማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑና የቀረበበትን የሰው እገታ ወንጀል ክስም ማስተባበል እንዳልቻለ ተናግረዋል።

በሰውና የሰነድ ማስረጃ  በማስደገፍ በግለሰቡ ላይ አቃቢ ህግ  የመሰረተበትን ክስ  የተመለከተው የወረዳው ፍርድ ቤት ጥፋተኝነቱን በማረጋገጥ ትናንት በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔውን ማስተላለፉን  አስታውቀዋል።

በወንጀሉ የተሳተፉ ቀሪ ተጠርጣሪዎችም ተይዘው ለህግ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ትዕዛዝ መስጠቱንም ባለሙያው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም