በአራዳ ክፍለ ከተማ ከ130 ሚሊዬን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ 48 ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኑ

62

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ በተያዘው በጀት ዓመት ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ 48 ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

ፕሮጀክቶቹን የአራዳ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎች፣ የክፍለ ከተማው አመራሮች እንዲሁም የፓርቲው አባላት ጎብኝተዋል፡፡   

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ኢንጂነር ያየ አማረ ለኢዜአ እንደገለጹት ክፍለ ከተማው ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን ለማጠናቀቅ  እየሰራ ነው፡፡

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ከተጀመሩት 51 ፕሮጀክቶች እስካሁን 48ቱ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀሪዎቹ ፕሮጀክቶች እስከ በጀት ዓመቱ መገባደጃ ድረስ ይጠናቀቃሉ ብለዋል፡፡

ለአገልግሎት ዝግጁ ከሆኑ ፕሮጀክቶች መካከል በትምህርት ቤቶች የተገነቡ 22 የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሾችና  እንዲሁም የማብሰያ ቦታዎች  እንደሚገኙባቸው  ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ሰባት የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች፣ የጤና ጣቢያ እድሳት፣ የወረዳ አስተዳደር ህንጻዎች እድሳትና በሶስት ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሶስት ዘመናዊ የመጸዳጃ ቤቶች ይገኙባቸዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሚደቅሣ ከበደ በበኩላቸው በፕሮጀክቶች መካከል በትምህርት ቤቶች ላይ የተገነቡት ግንባታዎች ፓርቲው ለመጪው ትውልድ ራዕይና ግብ መሳካት የሚሰራ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ እንደ ባህል ተደርጎ መወሰድ አለበትም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም