በረመዳን ወቅት ለሃገር አንድነትና ሰላም መስራትና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ይገባል- የስልጤ ዞን እስልምና ምክር ቤት

95

ሆሳዕና ፣ሚያዚያ 7/ 2013 (ኢዜአ) በታላቁ ረመዳን ወቅት ለሀገር ሰላምና አንድነት ጸሎት ማድረግ መተሳሰብ ከፈጣሪ ዘንድ በረከት የሚያሰጥ መሆኑን የስልጤ ዞን እስልምና ምክር ቤት ገለጸ።

ምክር ቤቱ በረካ ከተባለ የልማትና የበጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር ለሁለት መቶ አቅመ ደካሞች ለጾም ወቅት የሚሆን የእህል ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ በተሰጠበት ወቅት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼህ መሀመድ ሀሊል እንዳሉት በታላቁ ረመዳን ጾም ወቅት መተሳሰብ ለሀገር ሰላምና አንድነት ጸሎት ማድረግ ከፈጣሪ ዘንድ በረከት የሚያሰጥ ነው።

ከበጎ አድራጎት ማህበሩ ጋር በመቀናጀት ተንቀሳቅሰው መስራት ለማይችሉ አረጋውያንና ችግረኞች በአፍጥር ወቅት እንዳይቸገሩ ድጋፉ መደረጉን ገልጸው ህዝበ ሙስሊሙ የተቸገሩ ወገኖቹን በመደገፍና ለሀገር ሰላም ጸሎት በማድረግ ከጾሙ በረከት የሚያስገኝለትን ተግባር እንዲያከናውን ጠይቀዋል።

የበረካ ልማትና የበጎ አድራጎት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጅብሪል ኢብራሂም በበኩላቸው ማህበሩ የተቸገሩ ወገኖችን ከመርዳት ባለፈ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የተቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበሩ በረመዳን ወቅት ሰርተው መብላት የማይችሉ ወገኖችን ለመደገፍ ግለሰቦችን በማስተባበር ከምክር ቤቱ ጋር በጋራ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በድጋፉም ለእያንዳንዳቸው 25 ኪሎ ግራም የስንዴና በቆሎ ዱቄት የሾርባ እህልና አንድ ሊትር ዘይት መከፋፈሉንና ከ200 ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቁመዋል።

ድጋፉ ከተደረገላቸው መካከል በወራቤ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሙንተሃ አብዱልሀጂ እንደተናገሩት ወቅቱ ኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ተጽእኖ እያደረሰ የሚገኝበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ስራ ሰርተው ለጾሙ የሚሆን በቂ ነገር እንዳላስቀመጡ ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት በተደረገላቸው ድጋፍ እጅግ መደሰታቸውን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

አቅመ ደካማ በመሆናቸው ሰርተው ለጾሙ የሚሆን ለቤተሰቦቻቸው ማቅረብ እንዳልቻሉ የተናገሩት የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብድልከሪም አህመድ በበኩላቸው ጾሙን ሳይቸገሩ ለማሳለፍ እንዲችሉ ላደረጉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም