የመዲናዋ ወጣቶች ለምርጫው ሠላማዊነት ከማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጋር ተቀናጅተው ይሰራሉ

66

ሚያዚያ 6/2013 ከመዲናዋ ክፍለከተሞች ከእያንዳንዳቸው አንድ ሺህ ወጣቶች ተመልመለው ለምርጫው ሠላማዊነት ከማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጋር እንደሚሰሩ የአዲስ አበባ የወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ዙሪያ ለወጣቶቹ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ አካሂዷል፡፡

ቀደም ባሉት ምርጫዎች የተከሰቱ የጸጥታ መደፍረሶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ማስከተላቸውን ያስታወሱት ምክትል የቢሮ ኃላፊው አቶ ጥበቡ በቀለ በተለይ በወጣቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረው አልፈዋል ብለዋል።

የዘንድሮው ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ እንዲከናወን ወጣቶች በየአካባቢያቸው ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።


በቢሮው የወጣቶች ግንዛቤ ተሳትፎና ማካተት ዳይሬክተር ጤናዬ ታምሩ በበኩላቸው ወጣቶች ሰለምርጫው በቂ ግንዛቤ አግኝተው ለሠላማዊ ሂደቱ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ መድረኩ መዘጋጀቱን አውስተዋል።


ከየአንዳንዱ ክፍለከተማ አንድ ሺህ ወጣቶች ተመርጠው ለምርጫው ሠላማዊነት ከየአካባቢያቸው የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጋር እንዲሰሩ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በስራው ለሚሳተፉ ወጣቶች አስፈላጊ ግብዓት የማሟላትና የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራት እንደሚከናወኑም ጨምረው ገልጸዋል።


ምርጫው በሠላም እንዲከናወን ወጣቶች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዳይሬክተር ኮማንደር ሰለሞን ፋንታሁን ናቸው።

ወጣቶች ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የምርጫውን ሠላማዊ ሂደት ለማወክ የሚጥሩ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በየአካባቢያቸው ከሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት ለምርጫው ሠላማዊነት የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ወጣቶች በበኩላቸው ስለ ምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ምርጫን ተከትለው በሚፈጠሩ የሠላም መደፍረሶች ዋነኞቹ ተጎጂዎች ወጣቶች በመሆናቸው ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የየአካባቢያቸውን ሠላም መጠበቅ እንዳለባቸውም ለወጣቶች ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም