የአፍሪካ ድንገተኛ አደጋዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ስራ ጀመረ

73

ሚያዚያ 6/2013 (ኢዜአ) የአፍሪካ ድንገተኛ አደጋዎች ማሰልጠኛ ማዕከልን በአዲስ አበባ ኮቪድ-19 ፊልድ ሆስፒታል ለማስጀመር በጤና ሚኒስቴርና በዓለም ጤና ድርጅት የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ ሆነ።

በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት በዓለም የምግብ ፕሮግራም ድጋፍ የተገነባው የአዲስ አበባ የኮቪድ-19 የፊልድ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ደረጃውን የጠበቀ የአፍሪካ ድንገተኛ አደጋዎች ማሰልጠኛ ማዕከልን ስራ ማስጀመሪያ መርሀግብር ተካሂዷል።

በመርሀ ግብሩ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ሞኤቲ ሺዲን ጨምሮ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ዶክተር ሊያ እና  የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ሞኤቲ  ሺዲ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ የሚገኘውን የአፍሪካ ድንገተኛ አደጋዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ስራ አስጀምረዋል።

ማዕከሉ ኢትዮጵያ ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት የምታደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን ዶክተር ሊያ በዚሁ ጊዜ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ጠንካራ የድንገተኛ ሕክምና ስርዓት ለመፍጠር እንደሚረዳና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የድንገተኛ የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ማፍራት እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

ከዚህ ባሻገር በአፍሪካ ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ በመስጠት ረገድ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት እየመጡ ስልጠና በመውሰድ በአህጉሪቱ ጠንካራ የድንገተኛ ሕክምና ስርዓት የመፍጠር ሚናም ይኖረዋል ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ሞኤቲ  ሺዲ በበኩላቸው የማዕከሉ መቋቋም በድንገተኛ አደጋ ምላሽ ለመስጠት የባለሙያዎችን ክህሎት በማሻሻል አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ማዕከሉ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ብሄራዊ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ የመስጠት አቅምን ከማሳደግ በላይ በአፍሪካ ብሎም በዓለም የድንገተኛ አደጋ ምላሽ መስጠት የሚችል ቡድን እንዲለማ ያደርጋል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ የአሰልጣኞች ስልጠና ለተከታተሉ የሕክምና ባለሙያዎች የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ የችግኝ ተከላ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም