የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የፈጠራ ሥራዎች የህብረተሰቡን ችግር ለማቃለል የሚረዱ መሆን አለባቸው- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

70

ሚያዚያ 6/2013 (ኢዜአ) ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ባዛርና ኤግዚቢሽን "ሙያ ሃብት ነው'' በሚል መሪ ሃሳብ በጃን ሜዳ ዛሬ በይፋ ተከፍቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ መርሃ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል።

በንግግራቸውም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለህዝብ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን በማበርከት ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

አድካሚ የሆኑና በልምድ የሚከናወኑ ስራዎችን በተሻሻሉ አዳዲስ ፈጠራዎች በመተካት ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲያደርጉ ጠይቀው አስተዳደሩም የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በከተማዋ አሁን ላይ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከ26 ሺህ በላይ ባለሙያዎች በሥልጠና ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከተቋማቱ ባለፈው ዓመት ብቻ ከተመረቁት 6 ሺህ ተማሪዎች መካከል ከ4 ሺህ ለሚበልጡት የሥራ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ዳኛቸው በበኩላቸው ተቋማቱ የፈጠራ ስራቸው የማህበረሰቡ ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘርፉን ቴክኖሎጂ በመቅዳት ደረጃ በደረጃ የማሻሻል እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር ጥረቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከ13 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ድጋፍ እያገኙ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ የፊታችን እሁድ ድረስ በጃን ሜዳ በሚካሄደው ባዛርና ኤግዚቢሽን ማህብረተሰቡ በቦታው በመገኘት እንዲጎበኝ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በኤግዚቢሽኑ ላይ በ18 ዘርፎች ከ430 በላይ የተለያዩ ችግር ፈች የቴክኖሎጂ ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ ተመልካቶች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም