በመዲናዋ ከ8 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ

78

ሚየዚያ 6/2013(ኢዜአ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመዲናዋ ከ8 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ የተከሏቸውን ችግኞች በመንከባከብ መልካም ተግባር ላከናወኑ 14 ተቋማት እውቅና በመስጠት አመስግኗል።

በቀጣይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተቋማት በችግኝ እንክብካቤ ስራ ስለሚኖራቸው ተሳትፎም ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

ኮሚሽነሩ አቶ ሲሳይ ጌታቸው ባለፈው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመዲናዋ ከተተከሉ 8 ሚሊዮን ችግኞች 83 በመቶ ያህሉ መጽደቃቸውን ገልፀዋል።

በተለይም የፍራፍሬ ችግኞች መተከላቸው የከተማዋን ውበት ከመጠበቅ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በችግኝ ተከላው 426 ተቋማት መሳተፋቸውን ያስታወሱት ኮሚሽነር ሲሳይ 121 ተቋማት የተከሏቸውን ችግኞች የመንከባከብ ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህም ችግኞችን የተሻለ በመንከባከብ ለተመረጡ 14 ተቋማት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በመዲናዋ ከ8 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

ዕቅዱን እውን ለማድረግ የችግኝ ማፍላት ስራ በስፋት እየተከናወነ እንደሆነም አክለዋል።

ተቋማትም ከወዲሁ የሚተክሏቸውን ችግኞች በዘላቂነት መንከባከብ የሚያስችላቸውን ዕቅድ ከወዲሁ ማዘጋጀት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም