አካል ጉዳተኞች የምርጫ ካርዳቸውን መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል…የደቡብ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን

67

ዲላ  ሚያዝያ 6/2013 (ኢዜአ) አካል ጉዳተኞች ለቀጣዩ ምርጫ ተመዝግበው ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የደቡብ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጥሪ አቀረበ።

ፌዴሬሽኑ በክልል ደረጃ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት አካል ጉዳተኞች በመራጭነት እንዲመዘገቡ አድርጓል። 

በዚህ ወቅት ንግግር የደረጉት የደቡብ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ አሻግሬ “አካል ጉዳተኞችን ያላካተተ ምርጫ አሳታፊና ፍትሃዊ ነው ለማለት ያስቸግራል”ብለዋል።

ባለፉት ምርጫዎች በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት ተሳትፏቸው አነስተኛ እንደነበርም አስታውሰዋል።

አካል ጉዳተኞች ተመዝግበው ካርድ በመውሰድ ለአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጥ የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ምርጫ አስፈፃሚዎችም በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት የሚሳተፉ አካል ጉዳተኞች የዜግነት መብታቸውን እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እገዛ ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የአካል ጉዳተኛው የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት ሙሉ ለሙሉ የሚረጋገጠው በምርጫው ሲሳተፍና የዜግነት መብቱን ለመጠቀም ሲጠይቅ ነው የሚሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን አይነ ስውራን ልማት ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር ተሰማ ወሬራ ናቸው።

አካል ጉዳተኛው ድምፁን ይወክለኛል ለሚለው የፖለቲካ ፓርቲ ለመስጠት በመጀመሪያ የመራጭነት ካርድ መያዝ እንዳለበትም ተናግረዋል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ምርጫ ማስተባበሪያ በጎ ፈቃደኛ አቶ መንግስቱ ጌታቸው በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች ባሉበት ቦታ ሆነው ተወካዮቻቸውን የመምረጥና የመመረጥ ህገ መንግስተዊ መብት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዘንድሮው 6ኛ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ አካል ጉዳተኞች መብታቸውን በመጠቀም በምርጫው ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

እድሜያቸው ለመራጭነት የደረሱ አካል ጉዳተኞች የዚህ ታሪካዊ ምርጫ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማህበራት መሪዎች ግንዛቤ የማስጨበጥና የመቀስቀስ ሥራ መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም