ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘበ የአደጋ ስጋት የፖሊሲ ማዕቀፍና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው

87

ሚያዚያ 6/2013 (ኢዜአ) የአገሪቷን የዕድገት ደረጃና የስጋት ጫና ታሳቢ ያደረገ የአደጋ ስጋት የፖሊሲ ማዕቀፍና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ።

የአደጋ ስጋት ኮሚሽን መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመ ከ45 ዓመታት በላይ ቢሆንም የዘመኑን ዕድገት ታሳቢ ያደረገ የፖሊሲ ማዕቀፍና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ አልነበረም።

በመሆኑም የአደጋ ስጋት ስራ አመራር የፖሊሲ ማዕቀፍና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ሰነድ ማዘጋጀት አስፈልጓል እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ።

እየተዘጋጀ ባለው ሰነድ ላይም የመጀመሪያ ዙር ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሒዷል።

ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን እንደገለጹት በአገሪቷ ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት በአግባቡና በተደራጀ መንገድ ምላሽ ለመስጠት ችግሮች ያጋጥማሉ።

ችግሮቹ የሚያጋጥሙት አደጋ ሳይከሰት ለመከላከል፤ ከተከሰተም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ወቅቱን ያገናዘቡ ፖሊስና ስትራቴጂዎች የመተግበር ክፍተቶች በመኖራቸው ነው ይላሉ።

በመሆኑም የአገሪቷን ከተሞች ሁለንተናዊ እድገትና የገጠሩን ተጋላጭነት ታሳቢ ያደረገ ዘመናዊ የሪፎርም ሰነድ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

በዛሬው መድረክ ሰነዱን ለማበልፀግ በየደረጃው ከሚገኙ የተቋሙ የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተጨማሪ ሃሳብ የማሰባሰብ ስራ እየተካሔደ እንደሆነም አስረድተዋል።

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ተግባር ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ምክትል ኮሚሸነሩ ሰነዱን ለማበልፀግ የብዙሃኑ ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚዘጋጁ ጠቁመዋል።

የሠላም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ አጋርነትና ተጠሪ ተቋማት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ሻንቆ ደለለኝ እንዳሉት የአገሪቷ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ያለበትን ሁኔታ ለመፈተሽ የዳሰሳ ጥናቶች ተካሔደዋል።

በጥናቱም የአደጋ ስጋት ስራ አመራር አካሔዱ በውስን የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ ብቻ ያተኮረና ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን ማየት እንደተቻለ ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት ስራው ወቅቱን ያላገናዘበ በመሆኑም ይህንኑ መነሻ በማድረግ የፖሊሲ ማዕቀፍና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

በዳሰሳ ጥናቱ መነሻነት የተዘጋጀው የፖሊሲ ማዕቀፍና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ሁሉን አቀፍና አካታች መሆኑንም ጠቁመዋል።

ስትራቴጂው በአገር ደረጃ ደህንነቱ የተረጋገጠ፣ ለአደጋ ስጋት የማይበገርና የሕዝብ አመኔታ ያለው ተቋማዊ ልህቀት ማምጣት የሚያስችል እንደሆነም አውስተዋል።

በቀጣይም በመስኩ የተለያዩ አካላትን በማወያየትና ሕዝባዊ መድረኮችን በማዘጋጀት ግብዓት የማሰባሰቡ ተግባር እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም