የምርቶች ዋጋ ጭማሪ ችግር እንደሆነባቸው በጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

70

ጋምቤላ፤ ሚያዚያ 06/2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ በምግብና በግንባታ ምርቶች ላይ ተገቢ ባልሆነ የዋጋ ጭማሪ  መቸገራቸውን  አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በበኩሉ፤ በምርቶች ላይ ያለአገባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 51  የንግድ ቤቶች ላይ ህጋዊ  እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ አዳሙ ደበላ እንደተናገሩ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በዘይት፣ ዳቦ ዱቄት፣ ጤፍና ሽንኩርት ላይ ነጋዴው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል።

በተለይም የዳቦ ዱቄትና የምግብ ዘይት እጥፍ ሊባል በሚችል መልኩ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ጠቁመው መንግስት የዋጋ ንረቱን ለማርገብ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በከተማው በተለይም የሲሚንቶ ዋጋ ከእጥፍ በላይ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን እጥረት እንዳለ የተናገሩት ደግሞ  አቶ ሳሙኤል በቀለ ናቸው።

በዚህ ምክንያትም የጀመሩትን የህንፃ ግንባታ ስራ ለማቋረጥ መገደዳቸውን ገለጸው መንግስት በደላሎች አማካኝነት የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማርገብ መስራት አለበት ብለዋል።

ከንግዱ ማህበረሰብ መካከል አቶ ሲሳይ ደጀን በሰጡት አስተያየት በምግብ እህሎች ላይ የዋጋ ንረቱ የተከሰተው ተገቢ ያልሆነ ተደጋጋሚ የኬላ ቀረጥ፣ የአውራጅና ጫኝ ክፍያና ምርቱን ከሚያመጣበት አካባቢ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ ምክንያት ነው ብለዋል።

መንግስት ለዋጋ ንረቱ ምክንያት የሆኑትን በኩንታል የሃምሳ ብር ቀረጥና በኩንታል 30 ብር የሚደርስ የአውራጅና ጫኝ ክፍያ የሚስተካከልበት ሁኔታ ሊያመቻች እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይም የዘይትና ዳቦ ዱቄት ዋጋ ሊንር የቻለው  ከሚያመጡበት አካባቢ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የንግድ ማህበረሰብ  አቶ ራማቶ አዙሌ ናቸው።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮው ኃላፊ አቶ ቲቾት ኮመዳን እንዳስታወቁት፤ ተገቢ ያለሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 51 የንግድ ድርጀቶች የማሸግ እርምጃ  ተወስዷል።

እርምጃ የተወደባቸውም በኩንታል ጤፍ የ500 ብርና  በኩንታሉ ሲሚንቶ ላይ ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረው ከ550 ብር በላይ ጨምርው በመገኘታቸው ነው ብለዋል።

በሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉት ላይ ተመሳሰይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

በቀጣይም ተገቢ ያለሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደረጉ ነጋዴዎች ላይ  እርምጃ ለመውስድ ግብር ኃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቀረጥ፣ ከአውራጅና ጫኝ ጋር ተያይዞ በነጋዴዎች የተነሳው ቅሬታ አግባብነት ያለው መሆኑን ገልጸው ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም