በአዲስ አበባ የስርቆት ወንጀል በመባባሱ በየእለት እንቅስቃሴያችን ላይ ተቸግረናል

209

ሚያዝያ 6/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የስርቆት ወንጀል ተባብሶ በመቀጠሉ በየእለት እንቅስቃሴያችን ላይ ተቸግረናል ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ። 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በከተማዋ ያለውን የወንጀል ስጋት ለመቀነስ የፖሊስን ጥረት ህብረተሰቡ ማገዝ ይኖርበታል ብሏል።

ኢዜአ ያነጋገረቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ወጥቶ ለመግባት በሌብነትና ዝርፊያ የተሰማሩ ወንጀለኞች ስጋት ሆነዋል።

የወንጀል ድርጊቱ በየጊዜው እየተቀያየረ በርካቶች ንብረቶቻቸውን ማጣታቸውን በመጥቀስ "የወንጀል ድርጊት ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሰ መጥቷል" ይላሉ።

ወንጀለኞችን በማጋለጥና ከፖሊስ ጋር ተባብሮ በቁጥጥር ስር ለማዋል በርካታ ሰዎች ትብብር እንደማያሳዩም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የሚኖሩት የ70 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ አቶ ሁሴን አባተ፤ "ከተማዋን እያመሰ ያለው በርከት ያለ የስርቆት ወንጀል ሃይ ባይ ያጣ መስሏል" ብለዋል።

ወንጀሉን ለመከላከል የከተማው ነዋሪና ህግ አስከባሪው የተጠናከረ ትብብርና ቁጥጥር ካላደረጉ ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

በተለያዩ የስርቆትና ዘረፋ ወንጀል ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ወንጀለኞችም ተገቢና አስተማሪ ቅጣት ይገባቸዋል ብለዋል አቶ ሁሴን።

በአዲስ አበባ እየተባባሰ ለመጠው የስርቆት ወንጀል መበራከት አንዱ ምክንያት ወንጀለኞች ተገቢ ቅጣት አግኝተው ሳይታረሙ ከእስር እየተለቀቁ በመሆኑ ነው ይላሉ።

በዚህም ምክንያት ወንጀለኞች ከሳሹ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ስለሚያደርሱ በርካቶች ከመክሰስ ይልቅ ዝምታን፣ ወንጀለኛን ከማጋለጥ ይልቅ አይቶ እንዳላዩ የመምሰል አዝማሚያዎች እየታዩ መጥተዋል ብለዋል።

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ላይ ትኩረት ሲደረግ አጋጣሚውን በመጠቀም በአዲስ አበባም ህገ-ወጦች እየተበራከቱ ነው የሚለው ደግሞ ወጣት መጥምቁ ዮሃንስ ነው።

ከባንክ አካውንታቸው ሰዎች ገንዘብ እንዲሰጧቸው የሚያደርጉ የተደራጁ ወንጀለኞች መኖራቸውንም ጠቅሷል።

የስርቆት አፈጻጸሙም በተጠናና በተደራጀና ሁኔታ ከጥቃቅን ንብረቶች እስከ መኪና ስርቆት እየተበራከተ መጥቷል ነው ያለው።

በመሆኑም መንግስት እንዲሁም የፀጥታ ሃይሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ጥብቅ ቁጥጥር በማድርግ አስተማሪ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብሏል።

ሌላው የመዲናዋ ነዋሪ አቶ ሰውነት ደምሴ እንዳሉትም " በአንዱ ላይ ዛሬ የተፈፀመው ስርቆት ነገ በእያንዳችን ላይ ሊደርስ ስለሚችል ወንጀለኞችን ማጋለጥ በጋራም መከላከል ይጠበቅብናል" ብለዋል።

የሌብነት ወንጀልን መከላከል ለህግ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም ሊተባበር ይገባል ነው ያሉት።

ህግ አስከባሪዎችም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በከተማዋ ያለውን የወንጀል ስጋት ለመቀነስ የፖሊስን ጥረት ህብረተሰቡ በማገዝ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

በኮሚሽኑ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ በአዲስ አበባ ያለውን የወንጀል ስጋት ለመቀነስ ፖሊስ የተጠናከረ ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው የህብረተሰቡ ትብብር እንዳይለይ ጠይቀዋል።

ወንጀል ፈጻሚዎች ለህብረተሰቡ ቅርብና ከህብረተሰቡ የወጡም በመሆናቸው በትብብር ችግሩን መፍታት ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል።

በቅርቡም በህብረተሰቡ ትብብር በቡድንና በጦር መሳሪያ የታገዘ ዘረፈ ሲያካሂዱ የነበሩ ሰዎችን በቁጥጥር ማዋል ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም