በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መሰረቱ

61

ጋምቤላ፤ ሚያዚያ 06/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስድስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊና ሌሎች ጉዳዮች ተቀራርበው ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ ምክር ቤት መሰረቱ ።

ፓርቲዎቹ የጋራ ምክር ቤቱን የመሰረቱት  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ባመቻቸው መድረክ በቀረቡት የጋራ የመግባቢያ ሰነዶች ዙሪያ በመወያየት ከተፈራረሙ በኋላ ነው።

በክልል ደረጃ የጋራ ምክር ቤት ከመሰረቱት መካከል ጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ጋህነን/ ብልጽግና እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ ኢዜማ/ እና የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ/ጋህነዴን/ ይገኙበታል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከሁሉም ፓርቲዎች በእኩል የተወከሉ 30 አባላት ያሉት ሲሆን ለቀጣይ ስድስት ወራት የጋራ ምክር ቤቱን የሚመሩ ዋናና ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም ዋና ጸሐፊ በመምረጥ ተሰይመዋል።

ከምክር ቤቱ መስራቾች መካከል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ፤ምክር ቤቱ በክልሉ ብሎም በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮችና ሌሎች ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በተለይም የፈረሙት የመግባቢያ ሰነዶችን በማክበርና በማስከበር ረገድ ሁሉም ፓርቲ በአግባቡ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የሚኖሩ የጋራ አጀንዳዎችና የሚጋጠሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ፒተር አማን ናቸው።

‘‘ለክልላችንም ሆነ ለሀገራችን ያለናት እኛው ስለሆነን እንደ ፓለቲካ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ በያገባኛል ስሜት የህግ የበላይነትን እያከበርን በጋራ ልንሰራ ይገባል’’ብለዋል ።

ስድስትተኛው ጠቅላላ ምርጫም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በጋራ መስራት እንደሚገባም አቶ ፒተር አመልክተዋል።

የጋህፍሰልዴን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቾል ኮር በበኩላቸው ፤የጋራ ምክር ቤቱ ሊያጋጠሙ የሚችሉ ችግሮች በጋራ በመወያየት መፍትሄ ለመሻት ከፍተኛ ፋይዳ  እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢዜማ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ኮማንደር ጋድቤል ቦል የጋራ የምክር ቤቱ የመግባቢያ ሰነዶች ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ስጋቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ባመቻቸው የፓርቲዎች የጋራ መድረክ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአሠራር ደንብ፣ የቃል ኪዳን ሰነድ ለማስፈጸም የመጣውን የስነ ስርዓት ደንብ ጨምሮ አራት የመግባቢያ ሰነዶች በአመራሮቹ  ተፈርመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም