ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ ውይይት እያደረገ ነው

54

ሚያዚያ 06/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በአዲስ አበባ ውይይት እያደረገ ነው።

ውይይቱ የመራጮች ምዝገባ በምን አይነት መልኩ እየተካሄደ ነው? በሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮችን ምንድን ናቸው? የሚለውን መገምገም አላማ ያደረገ ነው።

የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ ስርጭትና ሂደት፣ የምዝገባው ተሳታፊዎች እንዲሁም ሎጀስቲክና ኦፕሬሽን ስራዎችን አስመልክቶ ቦርዱ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

በ673 የምርጫ ክልሎች በሚገኙ 49 ሺህ 407 የምርጫ ጣቢዎች ቁሳቁሶችን በማሰራጨት የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በውይይቱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ ከመጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ሲሆን ምዝገባው ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን 46 የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም