በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ውጤት ከአምናው የተሻለ ሆኖ ተመዘገበ

392
አዲስ አበባ ሃምሌ 24/2010 በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ውጤት ከአምናው የተሻለ ውጤት እንደተመዘገበበት የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ። የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ውጤት ዛሬ ከሰዓት ይፋ ሆኗል፡፡ በ2009 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመግቢያ ፈተና ከፍተኛው ውጤት 636 ሲሆን የዘንድሮ 649 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የ2010 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ተፈታኞች ውጤታቸውን በኤጀንሲው ድረገፅ www.naeae.gov.et  ማየት ይችላሉ። የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚሔር እንዳሉት በዘንድሮው አመት 281 ሺህ በላይ ተማሪዎች የተፈተኑ ሲሆን ዘጠና ስድስት ተማሪዎች 600 ነጥብ አምጥተዋል። ከተፈታኞቹ 52 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆኑት 350 እና ከዛ በላይ አስመዝግበዋል ነው ያሉት። ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች በአምስት ክልሎች የሚገኙ ተማሪዎች ናቸውም ብለዋል። የዘንድሮው ውጤት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በቁጥርም በውጤትም የተሻለ እንደሆነ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዱት። ውጤት የማረም ስራ በዘመናዊ መሳሪያ ታግዞ የተሰራ በመሆኑ በተማሪዎች ላይ ስጋት የሚያሳድር አለመሆኑን ገልፀዋል። በውጤቱ ላይ ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎች ከሰኞ ጀምሮ የኤጀንሲውን ድረ-ገፅ በመጠቀም አሊያም አራት ኪሎ በሚገኘው የኤጀንሲው ቢሮ በአካል በመምጣት ማቅረብ እንደሚችሉም ገልፀዋል። ወደ ዩንቨርሲቲ መግቢያ ወይም የመቁረጫ ነጥቡ ኤጀንሲው በቀጣይ በሚያቀርበው ፕሮፖዛል መሰረት በትምህርት ሚኒስቴር የሚወሰን እንደሚሆንም ነው ያስረዱት። ዘንድሮ 281 ሺህ 974 ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና መውሰዳቸውም ተገልጿል። የ10ኛ ክፍል ውጤትም ይፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ገብረእጊዘብሔር አንዳንድ መስተካከል ያለባቸው ስራዎች ሲጠናቀቁ ይፋ ይሆናል ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም