በነገሌ ምርጫ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ ቀረበ

94

ነገሌ ፤ ሚያዝያ 5 /2013(ኢዜአ) በጉጂ ዞን ነገሌ ምርጫ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን  ካርድ በየአቅራቢያቸው በተመቻቹ የምርጫ ጣቢያዎች ተመዝግበው ከወዲሁ እንዲወስዱ ጥሪ ቀረበ።

የምርጫ ክልሉ  አስተባባሪ አቶ አማኑኤል ብርሀኑ እንዳሉት፤ ለስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በቁሳቁስ መዘገየት ምክንያት በነገሌ ከተማ  የመራጮች ምዝገባ የተጀመረው ሚያዚያ 3/2013 ዓ.ም. ነው ፡፡

በከተማዋ በተቋቋሙት 21 ምርጫ ጣቢያዎች እስካሁን አንድ ሺህ 446 መራጮች ተመዝግበው ድምጽ ለመስጠት የሚያበቃቸውን ካርድ ወስደዋል ብለዋል፡፡

በምርጫ ክልሉ ስር በተደራጁ ዋደራ ሊበን ፣ጎሮዶላና ጉሚ ኤልደሎ ወረዳዎችም የመራጮች ምዝገባ መጀመሩንም  ጠቅሰዋል፡፡

ነገሌን ጨምሮ በወረዳዎቹ በተቋቋሙ 139 ምርጫ ጣቢያዎች ከ200 ሺህ በላይ ህዝብ በመራጭነት እንደሚመዘገብ የሚጠበቅ መሆኑን ነው አስተባባሪው የገለጹት፡፡

በምርጫ ክልሉ የሚኖረው ህዝብ እራሱንና የምርጫ አስፈጻሚዎችን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ለመከላከል ጥንቃቄ በማድረግ በየአቅራቢያቸው በተመቻቹ የምርጫ ጣቢያዎች እየቀረበ በመመዝገብ  ከወዲሁ ካርድ  እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የነገሌ ከተማ ቀበሌ ሶሰት  ነዋሪ ወይዘሮ ሶፊያ ሰይድ በሰጡት አስተያየት፤  ሰላም አንድነትና እኩልንትን በማስፈን ለሀገር የሚሰራ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ስህን ጥላሁን በበኩላቸው፤ በሀገር አቀፉ ምርጫ ድምጽ የሚሰጠው በህግ የበላይነትን ለሚያምን ፓርቲና እጩ ተወዳዳሪ ነው ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመቻቻልና መከባበር ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በስድስተኛው  ጠቅላላ  ምርጫ  ላይ ለመሳተፍ የመራጮች ምዝገባ  ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ  ከመጋቢት 16 እስከ ሚያዚያ 15/2013 ዓ.ም. ድረስ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወቅቱ ይፋ አደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም