የጅማ ቤተመንግስት እድሳትና የተጨማሪ ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት 98 በመቶ ተጠናቀቀ

74

ጅማ፤ ሚያዝያ 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) የጅማ ዘመናዊ ቤተ መንግስት እድሳትና አዲስ የተጨማሪ ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት 98 በመቶ መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ገለጹ።

ስራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ ከ243 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ከሶስት ዓመታት በፊት የተጀመረ ነው።

የቤተመንግስቱን እድሳትና አዲስ የተጨማሪ ህንጻዎች ግንባታ ቀሪ ስራ የመዋኛ ገንዳ ማጠቃለያ ብቻ እንደሆነ አመልክተው፤ የፕሮጀክቱ 98 በመቶ ስራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በአዳዲስ ሁለት ዘመናዊ አፓርታማዎች የእንግዳ ማረፊያዎች፣ ለጂም እና ካፌ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች፣ የመዋኛ ገንዳዎችና ሌሎችንም መገልገያ ህንጻዎች ግንባታ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

ነባሩ ቤተ መንግስትን ጨምሮ የጊቤ አዳራሽ፣ ማብሰያ ቤቶች፣ መናፈሻዎች፣ የሰራተኞች ማረፊያ፣ የጋራዥና የመጋዘን እድሳት ስራዎች ቅርስነታቸውን ሳይለቁ መታደሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

እድሳትና ግንባታው ከዕቅዱ አንጻር መዘግየቱን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፤ የግንባታ ዕቃዎች ከገበያ መጥፋት ለመዘግየቱ መንስዔዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ስራውን በማፋጠን ቀሪው የመዋኛ ገንዳ ስራ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት ለበርካታ ሰዎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ ስንታየው ግርሻው በበኩላቸው፤ የተሰሩት ህንጻዎች ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን በክትትልና ቁጥጥር ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

“ፕሮጀክቱ ከሳምንት በኋላ ተጠናቆ ርክክብ ይካሄዳል” ብለዋል።

የቤተ መንግስቱ አስተዳደር አስተባባሪ ተወካይ ወይዘሮ ካሴች ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ የህንጻዎቹ መገንባትና የእድሳት ስራው መጠናቀቅ ለአካባቢው ውበት ሰጥቷል፡፡

ዘመናዊውን ቤተ መንግስት ያሰሩት ደጃዝማች ጸሀይ እንቁስላሴ የከፋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ እንደነበሩ ያስታወሱት ወይዘሮ ካሴች፤ “ቦታው ታሪካዊና ዘመናዊ መዝናኛ ለመሆን በቅቷል” ብለዋል፡፡

በጅማ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቅርስ ባለሙያና የጅማ ሙዚየም ሀላፊ አቶ ነጂብ ራያ “ፕሮጀክቱ የከተማችንን የቱሪዝም ዘርፍ ያሳድገዋል” ብለዋል፡፡

በጅማ ከተማ የሚገኙ በርካታ መስህቦችን በበለጠ እንዲጎበኙ እድል የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከአሁን ቀደም በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ የእንግዳ ማረፊያ ያለመኖር የጎብኝዎች ችግር ሆኖ ሲነሳ የቆየ መሆኑን አቶ ነጂብ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም