በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው

70

ሚያዚያ 5/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የአገሪቱን ሁሉንም አካባቢዎች በሚዳስሰው ጥናት ዕድሜያቸው ከ15 በላይ የሆኑ 13 ሺህ 600 ሰዎች የጥናቱ አካል እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

በ25 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚካሄደው ይኸው ጥናት ከሚያዝያ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለ30 ቀናት እንደሚከናወንም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

በጤና ሚኒስትር የሚመራው ኮቪድ 19 የክሊኒካል አማካሪ ቡድን አባል ዶክተር አበባው ገበየሁ ጥናቱ  በኮቪድ-19 ያለውን መረጃ ያጠናክራል ብለዋል።

አሁን ላይ የቫይረሱ ስርጭት በስፋት የሚታይባቸውን አካባቢዎች በመለየትና በስፋት የተጠቃውን የዕድሜ ክልልም ለማወቅ ያስችላል ነው ያሉት።

ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመለየትና ለነዚህም የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ ጥናቱ ወሳኝ መሆኑን ዶክተር አበባው ተናግረዋል።

ጥናቱ ወቅታዊ የቫይረሱ ስርጭት ያለበትን ደረጃ ለመተንተንና አገራዊ ምላሹን ለማጠናከር እንደሚውል ተናግረዋል።

ጥናቱ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን በመግታት በኩል የጥንቃቄ መመሪያዎችን እንዲተገብሩ አሳስበዋል።  

ጥናቱን የሚያከናውኑ 160 መረጃ ሰብሳቢዎች ዛሬና ነገ ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ትናንት ብቻ 28 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ አሁን ላይ 983 ሰዎች በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 230 ሺህ 944 ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም