በጉጂ ዞን በ2ተኛው ዙር መስኖ ከ4ሺህ ሔክታር መሬት በላይ ለምቷል

68

ነገሌ  ሚያዝያ 5/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በ2ኛው ዙር መስኖ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአትክልትና ስራስር ምርቶች መሸፈኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ሊበን ቦሩ እንዳሉት በተያዘው በጋ ወራት ለ2ኛው ዙር የመስኖ ልማት 6 ሺህ 440 ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል፡፡

ከዚህ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ 4 ሺህ 220 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የገለጹት ባለሙያው፣ በዚህ ልማት 21 ሺህ 275 አርብቶ አደሮች መሳተፋቸውንም ጠቁመዋል።

ከነዚህ ተሳታፊዎች መካከልም 1 ሺህ 815 ሴቶች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

ይህ 4 ሺህ 220 ሄክታር መሬት በካሮት፣ በሽንኩር፣ በቀይ ስር፣ በድንች፣ በቲማቲም፣ በአበሻ ጎመን፣ በሰላጣ፣ ቆስጣና የሀበሻ ጎመን የተሸፈነ መሆኑም ተገልጿል።፡፡

ለምርት ማሳደጊያ የሚሆን 400ኩንታል ማዳበሪያን ጨምሮ አስፈላጊው የምርጥ ዘር አቅርቦትም መሟላቱን ገልጸው ከ2ኛው ዙር መስኖ ልማት ከአንድ ሚሊዮን 400 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የሰባቦሩ ወረዳ ነዋሪ አቶ ደምሴ ኦዳ እንዳሉት ከሻኪሶና አዶላ ከተሞች የሚገዙትን የአትክልትና ስራስር ምርት በአካባቢያቸው ማግኘት እንዲቻል ካለፈው አመት ጀምሮ የመስኖ ልማት ስራ ጀምረዋል፡፡

በተያዘው አመት 6 ሄክታር መሬት ለማልማት ቢያቅዱም ከእንስሳት እርባታ ሌላ ልምድ ስለሌላቸው እስከ አሁን በአትክልትና ስራ ስር ዘር የሸፈኑት ሁለት ሄክታሩን ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አሁን ባገኙት ግንዛቤ አትክልትና ስራ ስር በስፋት በማልማት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፈው ለገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ አብዲ ቦሩ በቂ የከርሰ ምድር ውሃ ቢኖርም በገንዘብ አቅም ማነስ እስከ አሁን የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን በቁጭት ይገልጻሉ፡፡

በመጀመሪያው ዙር ከግማሽ ሄክታር ያገኙትን 30 ኩንታል ምርት ለማሳደግ የሚያለሙትን መሬት በመጨመር የተሻለ ምርት የመሰብሰብ እቅዳቸውን ለማሳካት እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በመጀመሪያው ዙር በመስኖ ከለማው 16 ሺህ ሄክታር መሬት እስከ አሁን ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ምርት መሰብሰቡ ተመልክቷል።፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም