ብልጽግና ፓርቲ በገንዳውሃ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳና የዕጩዎች ትውውቅ መረሃ ግብር አካሄደ

64

መተማ ሚያዚያ 05/2013 (ኢዜአ) ብልጽግና ፓርቲ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውሃ ከተማ አባላቱና ደጋፊዎቹ በተገኙበት በጎዳና ላይ የምረጡኝ ቅስቀሳና ዕጩዎች ትውውቅ መረሃ ግብር አካሂደ።

በመረሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሃላፊ አቶ ሆናለም አሻግሬ እንደተናገሩት፤ ስድስተኛ ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሚጣልበት እንዲሆን  አበክረው እየሰሩ  ነው።

ህዝቡ ይወክለኛል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ በአግባቡ ተረድቶ በነፃነት በመምረጥ ለሀገር እድገትና ብልፅግና ተጠናክሮ መቀጠል የበኩሉን እንዲወጣ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ምርጫው ህብረተሰቡ በነጻነት የሚፈልገውን ፓርቲ የሚመርጥበት እንዲሆን በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብረው እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

ከፓርቲው አባላት መካከል ወጣት ግዜው አለምነው በሰጠው አስተያየት ፤ መጪው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች  አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ተናግሯል

እንደ ብልጽግና አባልነቱ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ጋር በጋራ በመሆን በሰላማዊ ምርጫና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚሰራ ገልጿል።

የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ  አቶ ተስፋሁን ሲሳይ በበኩላቸው ፤በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ለማድረግ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ህዝቡ  የምርጫ ካርዱን በማውጣት የሚወክለውን መምረጥ ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም