በመተከል ዞን የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው -- አቶ አሻድሊ ሀሰን

65

ሚያዚያ 5 /2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

የፌዴራልና ክልል የስራ ሃላፊዎች በመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ጋር በዞኑ ዋና ከተማ ግልገል በለስ ተገኝተው ውይይት አድርገዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ከውይይቱ በኋላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የመተከል ዞንን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ የተቀናጁ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

የዞኑ የተቀናጀ ግብረሃይል የአካባቢውን ሰላም በማጠናከር የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው በመመለስ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

"የታጠቁ ሽፍቶችን የማደን ስራው እንዳለ ሆኖ ወደ ሰላማዊ ድርድር የሚመጡትንም ተቀብሎ በሰላማዊ አማራጭ የመቋጨት ስራ ይከናወናል" ያሉት አቶ አሻድሊ፤ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ስራ በትኩረት እንደሚከናወንም አረጋግጠዋል።

ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው የግብርና ስራቸውን በወቅቱ እንዲያከናውኑ ለማስቻል የፌዴራልና የክልሉ መንግስት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በዞኑ እየተከናወነ ባለው ሰላምና ማረጋጋት እንዲሁም የተፈናቀሉትን በመመለስ ሂደት እንቅፋት የሚፈጥሩ አመራሮች ላይ ቀደም ሲል እርምጃ መወሰዱን አስታውሰው፤ እርምጃ መውሰዱ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም