በሕዳሴ ግድብን ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶች መፈታት ያለባቸው በውይይት ነው--የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

53

ሚያዚያ 5/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው የህዳሴ ግድብ ላይ የሚስተዋሉ አለመግባባቶች  መፈታት ያለባቸው  በመነጋገር ብቻ መሆን  እንደሚገባው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ሰርጌ ላቭሮቭ ገለጹ ፡፡

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት  ትላንት ከግብፅ አቻቸው  ሳሜህ  ሽኩሪ  ጋር በካይሮ ባካሔዱት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

በመግለጫቸውም "ልዩነቱ እንዲስተካከል ሩሲያ ጽኑ ፍላጎት አላት፣ በተለይ ሶስቱ ሃገራት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ሃገራቸው የቴክኒክ ድጋፍ ታደርጋለች " ብለዋል፡፡

ልዩነቱ መፈታት ያለበትም በውጭ አካላት ሳይሆን በራሳቸው  ሶስቱ ሀገራት ብቻ  መሆን እንዳለበት  አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

ድርድሩም በአፍሪካ ህብረትና  ማዕቀፍ እና  በሶስቱ ሃገራት ብቻ መታየት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለም ለድርድሩ ስኬታማነት  የሩስያ አመራሮች እንዲሁም  የሃይድሮ  ኤሌክትሪክ ባለሙያዎች በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

ሩሲያ የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን ችግሮችን በራሳቸው እንዲፈቱ ታበረታታለች ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም