በአዲስ አበባ እስካሁን ከ72 ሺህ 600 በላይ ሰዎች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ወስደዋል

118

ሚያዚያ 4 /2013 (ኢዜአ) በመዲናዋ እስካሁን ከ72 ሺህ 600 በላይ የህክምና ባለሙያዎችና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት መውሰዳቸውን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የአዲስ አበባ ከተማን የክትባት አሰጣጥ በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ክትባቱን የተመለከቱ አንዳንድ የተዛቡ አመለካከቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለ ከተሞች ለ38 ሺህ 475 የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ክትባቱን ለመስጠት መታሰቡን ጠቅሰው፤ እስካሁን ለ27 ሺህ 109 ሰዎች መዳረሱን ተናግረዋል።

ከህክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪዎች በተጨማሪ ከ44 ሺህ ለሚበልጡና እድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ክትባቱ መዳረሱን ገልጸዋል።

በመዲናዋ እስካሁን በድምሩ 72 ሺህ 646 የህክምና ባለሙያዎችና ለኮቪድ-19 ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን መውሰዳቸው ታውቋል።

በመድረኩ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በቢሮው የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ቤተልሄም ታዬ እንዳሉት፤ ክትባቱ እንደማንኛውም ክትባት ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካምን የመሳሰሉ ምልክቶችን ከማሳየት ባለፈ የተለየ ጉዳት አያስከትልም።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ኮቪድ-19 እያደረሰ ያለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት መንግስት በከፍተኛ ጥረት የኮቪድ-19 ክትባት ማስገባቱን ገልጸው፤ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መከተብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የእምነት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የሚመለከታቸው አካላት ህብረተሰቡ ክትባቱን እንዲወስድ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም