የህዝቦችን አብሮነት ለማደፍረስ የሚጥሩ ኃይሎችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ተጠቆመ

78

ሚያዚያ 4/2013 (ኢዜአ) የህዝቦችን አብሮነት በማደፍረስ የጥፋት ተልእኮ ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በጋራ መታገል አለብን ሲሉ በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ተቋማት ጉዳዮች ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ ተናገሩ።

ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው አስተዳደር የጥቂት ቡድኖችን ስልጣን ለማቆየት ሲባል የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት አደጋ ላይ የሚጥል ልዩነት ሲሰበክ መኖሩንም ገልጸዋል።

አሁን ላይ በተለያዩ አከባቢዎች የምናያቸው የሰላም መደፍረሶችም የዚሁ ዘር ፍሬ መሆኑን ዶክተር አለሙ አብራርተዋል።

በመተከል የታየው የሰላም መደፍረስም ልዩነትን መሰረት ተድርጎ  የተረጨ መርዝ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የህዝቦችን አብሮነት በማደፍረስ ለ27 ዓመታት የተሰራበትን የጥፋት ተልእኮ ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በጋራ መታገል አለብን ብለዋል።

በመተከል ዞን ይህንን እኩይ አላማ ይዞ በሚንቀሳቀሰው ሃይል ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድና ወደ ሰላም ለማምጣት የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ፤ የብዝሃ-ማንነት ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ የዜጎችን አብሮነትና አንድነት የማጠናከር አላማ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያዊያን በጋራ የገነባነው ሀገር፣ ታሪክና ማንነት አለን" ሲሉም ነው የተናገሩት።

በመሆኑም በልዩነት መርዝ የህዝቦችንን አብሮነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ሃይሎችን በጋራ መታገልና የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ አለብን  ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም