አዲሱ የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ የጠበቆች ማህበር ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ ያግዛል--ጠቅላይ አቃቤ ህግ

510

ሚያዚያ 4/2013 (ኢዜአ) አዲሱ የፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ የጠበቆች ማህበር ህጋዊ የሰውነት እንዲያገኝ የሚያግዝ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ የህዝብ ውይይት መድረክ ዛሬ አካሂዷል።

በመድረኩ የፌዴራል ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተስፋዬ ዳባ ረቂቅ ህጉን ማዘጋጀት ያስፈለገባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረዋል።

ነጻ የጥብቅና አገልግሎት መለኪያ አለመቀመጡ፣ ባልታደሰ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ጠበቆችን መቆጣጠር የሚቻልበት አሰራር አለመኖርና ፈቃድ አለማሳደስ እንዲሁም ሌሎች ችግሮች ረቂቀ አዋጁ እንዲዘጋጅ ማድረጋቸውን ነው ያብራሩት።

ጠበቆች በፍትህ ስርአቱ ውስጥ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ያላቸውን ሚናም አስረድተዋል።

ጠበቆች የሙያ ስነ-ምግባራቸውን ጠብቀው መስራት እንዳለባቸው ረቂቅ አዋጁ ያስገድዳል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ።

የጠበቆች ማህበር የበለጠ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ ጠበቆች መብትና ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ እንደሚያግዛቸውም ጨምረው ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ ጠበቆችን በሚመለከት ቀደም ሲል በመንግስት በኩል ሲደረግ የነበረው የስነ-ምግባርና ሌሎች ጉዳዮችን በማህበሩ እንዲታይ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችም ተናግረዋል።

ረቂቅ አዋጁ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለማህበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግበት አስገዳጅ አሰራር እንዳለውም  አስገንዝበዋል።

ጠበቆች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግም ልማዳዊ አሰራሮችን ያስቀራልም ነው ያሉት።

እንደአጠቃላይ አዲሱ የፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ የጠበቆች ማህበር ህጋዊ የሰውነት እንዲያገኝ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

በመድረኩ ጠበቆች የህግ ስልጠና የመውሰድ ግዴታ፣ ግብር፣ ምዝገባና ፈቃድ እድሳት፣ የዲሲፕሊን ጥፋትና ቅጣት፣ የፌዴራል ጠበቆች ማህበር ማቋቋምና ሌሎች ድንጋጌዎችን የተመለከቱ አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል።

አስተያየቶቹ እንደ አስፈላጊነታቸው መጠን ለረቂቅ ህጉ በግብዓትነት ይታያሉ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም