ማህበረሰብ አቀፍ ትስስርና ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ወሳኝ ናቸው- የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን

171
አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 ማህበረሰብ አቀፍ ትስስርና ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ስኬታማነት ወሳኝ መሆናቸውን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አስታወቀ። በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ዙሪያ ያተኮረና ፍትሐዊ  የአገራት ንግድ ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ መር ጉዞና ውህደት በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው ሁለተኛው ዙር ስብስባ ባለፈው ሳምንት በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ ተካሂዷል። ስብሰባው እ.አ.አ በ2016 በአፍሪካ ያለውን የመንግስት፣ የህዝብና የግሉ ዘርፍ ግንኙነት በማጠናከር የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተግባራዊነት እንዲፋጠን ማድረግ አላማን ይዞ የተጀመረው ተከታታይ የውይይት መድረክ አካል መሆኑን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በአፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ማሳለጥና ማጠናከር የሚያስችሉ ሀሳቦችን በማቅረብ እንዲሁም ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ዙሪያ እስካሁን የተካሄዱ ምክክሮች የተገኙ ሀሳቦችና ስምምነቱ አሁን ያለበትን ደረጃ ለባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅ የስብሰባው ዓላማ ነው። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት የስራ ኃላፊ ፕሩደንስ ሴብሀይዚ እንደገለጹት ስምምነቱን አስመልክቶ የሚካሄዱ የባለድርሻ አካላት ውይይቶች በአህጉሪቷ የሚገኙ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ለሚያነሷቸው ሀሳቦች ምላሽ ከመስጠት አንጻር ጠቀሜታው የጎላ ነው። በየአገራቱ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ስምምነትን አስመልክቶ ጠንካራ ውይይት በየቀጠናውና በአጠቃላይ በአህጉር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ተከታታይ ውይይቶች ካልታገዘ ስምምነቱ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል። በዚህ ረገድ ማህበረሰብ አቀፍ ትስስርና ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ስኬታማነት ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ሲወያዩ እንደነበር የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስታውቋል። በውይይቱ ላይ የቀረቡ ሀሳቦችና ጥናታዊ ጽሁፎች በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለአካዳሚ ባለሙያዎች፣ ለሲቪክ ማህበረሰብ ተዋናዮችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሰራጭም ተጠቅሷል። ሰኔ 24 እና 25 ቀን 2010 ዓ.ም በሞሪታኒያ ርእሰ መዲና ናውክቾች በተካሄደው 31ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እስካሁን 49 አባል አገሮች ነጻ የንግድ ቀጠናውን ለመመስረት የሚያስችለውን ሰነድ ተቀብለው በፊርማቸው ማጽደቃቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ስምምነቱን ከፈረሙት 49 የአፍሪካ አገራት ውስጥ 22ቱ በፓርላማቸው በማቅረብ ሲያጸድቁ ስምምነቱ ተግባራዊ ይሆናል። ኬንያና ጋና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ለመተግበር የመጨረሻውን ስምምነት ያጸደቁ የመጀመሪያዎቹ አገራት ናቸው። የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት በአፍሪካ አጀንዳ 2063 ከተያዙ ግንባር ቀደም ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን፥ አፍሪካዊያንን በኢኮኖሚ ውህደት ብልፅግናቸውን ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ እድል ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። የአፍሪካ አገሮች የፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማትና የእቅድ ሚኒስትሮች በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ በስምምነቱ ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ለማጽደቅ ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸው ነበር። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ሲተገበርም ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የመሳብ እድሏ እንደሚጨምርም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም