የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ከሁዋዌይ ጋር መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሠነድ ተፈራረመ

78

ሚያዚያ 4 / 2013 (ኢዜአ) የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን በኢትዮጵያ የመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ተሰጥዖ ምህዳር ለማልማት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሠነድ ከቻይናው ሁዋዌይ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።

የመግባቢያ ሠነዱን የተፈራረሙት የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁንና በኢትዮጵያ የሁዋዌይ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቼን ሚንግሊያን ናቸው።

በሥምምነቱ መሰረት ተመራቂ ተማሪዎች በሁዋዌይ ኩባንያ በሚቀርበው ነጻ ሥልጠና ተጠቃሚ በማድረግ ያላቸውን ክህሎት እንዲያዳብሩ ያስችላል ተብሏል።

በዚህም የሁዋዌይ ኩባንያ በሦስት ዓመታት 4 ሺህ ተመራቂ ተማሪዎችን በማሰልጠን የእውቅና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።

ከእነዚህ ውስጥ ኩባንያው ለ400 ተማሪዎች የሥራ እድል እንደሚያመቻችም ጭምር ተገልጿል።

የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን በዚሁ ጊዜ የግል ዘርፉ ተሳትፎ የሥራ እድሎችን ለማስፋት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

“ግዙፉ የቴሌኮም መሰረተ ልማት አቅራቢ ኩባንያ ሁዋዌይም ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች እውቀትና ልምዳቸውን ለማጎልበት አስተዋጽዖ የላቀ ነው” ብለዋል።

ኩባንያው የሚሰጠው ክህሎትና የእውቅና ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው ነው የተናገሩት።

“በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት በማቃለልም የጎላ ሚና አለው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሁዋዌ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቼን ሚንግሊያን በበኩላቸው ኩባንያቸው ያለውን ክህሎት ለኢትዮጵያዊያን ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ክላውድ ኮምፒውቲንግ የመሰሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ኩባንያቸው ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

በዚህም ዘርፍ የሰለጠኑ ምሩቃንና ባለሙያዎች በቴሌኮም አቅራቢ ኩባንያዎች ተፈላጊነታቸውን በመጨመር ረገድ እገዛ እንደሚያደረግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም