ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአጼ ቴዎድሮስን የታሪክ አሻራ ስፍራዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት አዘጋጀ

150

ጎንደር ፤ ሚያዚያ 4/2013(ኢዜአ) ጎንደር ዩንቨርሲቲ የአጼ ቴዎድሮስን የታሪክ አሻራ ስፍራዎችን በመጠበቅና በመንከባከብ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል የአምስት ዓመት የልማት ፕሮጀክት ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

እስከ 280 ሚሊዮን ብር የሚጠይቀው ፕሮጀክት 8ሺህ ለሚሆኑ ወገኖችም የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚያስችል በፕሮጀክቱ ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር ላይ ተመልክቷል።

በዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ታያቸው እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ "የቋራ መቅደላ ማህበረሰብ አቀፍ ኢኮ ቱሪዝም" በሚል ስያሜ የሚተገበር ነው።

በፕሮጀክቱ ከአጼ ቴዎድሮስ የትውልድ ስፍራ ቋራ ጀምሮ ለሀገር አንድነት ሲሉ መስዋዕት የሆኑበትን የመቅደላ አምባ የሚደርሱ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ቋራን፣ ደረስጌ ማርያምን፣ ጋፋትንና መቅደላን ያካተተው ፕሮጀክቱ የአጼ ቴዎድሮስን ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ አሻራ የሆኑትን ቅርሶች በመጠበቅና በመንከባከብ አለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ዓላማ ያደረገ ነው።

የአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ እሴቶች የሆኑ ታሪካዊ ስፍራዎቹ በቂ ጥበቃና ትኩረት የተሰጣቸው ባለመሆኑ ቅርሶቹ ለአደጋ የተጋለጡበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የአካባቢዎቹን ስነ-ምህዳር መሰረት በማድረግ ታሪካዊ ስፍራዎቹን ጥንታዊ ገጽታ የመጠበቅና የተፈጥሮ ሀብቱን የማልማት ስራ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ወደ ታሪካዊ ስፍራዎቹ የሚያስገቡ የመንገድ መሰረ ልማቶችን ከመገንባት ጀምሮ የቱሪስት መዝናኛዎች በማሟላት ዋነኛ የቱሪስት መዳራሻ ስፍራ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

አራቱን ታሪካዊ ስፍራዎች በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለማልማትና ለመጠበቅ በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሚሳተፉበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ገለጻ የፌደራልና የአማራ ክልል መንግስታት፣ የማእከላዊ የሰሜን የምዕራብና የደቡብ ጎንደር እንዲሁም የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደሮችና ህብረተሰቡ በፕሮጀክቱ ትግበራ ይሳተፋሉ፡፡

በቀጣዩ ዓመት ወደ ትግበራ የሚገባው ፕሮጀክት እስከ 280 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ነው ያሉት አስተባባሪው የገቢ ማስገኛ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ወጪውን ለመሸፈን መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ እስከ 8ሺህ ለሚደርሱ የአካባቢዎቹ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

"አጼ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ካስጠበቁ ታላላቅ የሀገሪቱ መሪዎች አንዱ ናቸው" ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራሙ የቱሪዝም ሀብት ልማትን ማጠናከር የቅርስ ክብካቤን መደገፍ፣ ቅርሶችንና ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ማስተዋዋቅ ዋና ዓላማ በማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።

የአጼ ቴዎድሮስ ፕሮጀክት በክልል ደረጃ ብቻ ሳይሆን ሀገር አቀፍ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለተፈጻሚነት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር የታሪክና የቱሪዝም ምሁራን፣ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሃላፊዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም