በኩስሜ ብሔረሰብ መካከል ተከስቶ የነበረው አለመግባባት በእርቀ ሠላም እልባት አገኘ

93

አርባ ምንጭ ፤ ሚያዚያ 04/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ደራሼ ወረዳ ለዘመናት አብረው በኖሩ የኩስሜ ብሔረሰብ መካከል ተከስቶ የነበረው አለመግባባት በእርቀ ሠላም እልባት አገኘ።

በወረዳው በተካሄደው እርቀ ሠላም ስነ-ስርዓት የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ እንዳሉት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፀረ- ሰላም ኃይሎች ሴራ የዜጎች ህልፈት፣ መፈናቀልና ንብረት ውድመት አስከትሏል።

በተለይ በብሔር፣ ቋንቋና ባህል አንድ የሆነውን ህዝብ በጎሳና በመንደር በመከፋፈል ለጥፋት የተሰለፉ አካላት ዜጎችን ለጉዳት ሲዳርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በደራሼ ልዩ ወረዳም በተመሳሳይ መልኩ ለዘመናት አብረው ከሚኖሩ አራት ብሔረሰቦች መካከል የኩስሜ ብሔረሰብ አባላት ከጥር ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ጥፋት ህዝቡ ተረጋግቶ እንዳይኖርና የተጀመረው ልማት እንዳይቀጥል በማድረግ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት እንዲናጋ አድርጎት ቆይቷል ብለዋል።

ይህም ሆኖ በአካባቢው  አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍንና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ የሰላም ወዳዱ ህዝብ ሚና የላቀ እንደነበር አስታውሰው በተለይ ችግሩ በእርቅ ሰላም እልባት እንዲያገኝ የፀጥታ አካላት፣ ሃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።


አጥፊ የሆነ አስተሳሰብና ተግባር ተመልሶ እንዳይመጣ ህዝቡ በታረቀው ልክ የቀድሞውን አንድነት በማጠናከር ለአካባቢው ሰላም ዘብ እንዲቆም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደራሼ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አመኑ ቦጋለ በበኩላቸው በወረዳው የሚገኙ የደራሼ፣ ኩስሜ፣ ማሾሌ እና ሞሲዬ ብሔረሰብ ህዝቦች በወንድማማችነት እሴት በፍቅርና በመቻቻል ሲኖሩ የነበሩ መሆናቸውን አውስተዋል።

ሀገራዊ ለውጡ ተከትሎ እንደሌላው አካባቢ ሁሉ በደራሼ ልዩ ወረዳ የሚገኘው የኩስሜ ብሔረሰብ ህዝብም በከተማ አስተዳደር የመደራጀት፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ማንሳቱን ጠቅሰዋል።

የህዝቡ ጥያቄ በህጋዊ መንገድ እንዳይታይ ፀረ- ሰላም ሃይሎች ጣልቃ በመግባት በወረዳው ጋቶ ቀበሌ መንደር አንድ እና መንደር ሁለት የሚኖረውን የኩስሜን ህዝብ ለሁለት በመከፋፈል ለችግር እንዲጋለጥ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው አመፅ ካልተነሳ የህዝብ ጥያቄ አይመለስም በሚል የተሳሳተ አካሄድ  ህብረተሰቡን አለማግባባት ወስጥ በማስገባት የሰው ህይወትና ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት እንዲጠፋ ማድርጋቸውን አመልክተዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ፤ የኩስሜ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ወደ ቄየው በመመለስ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል፤ ያለፈውን በመርሳት ወደ ልማት መሄድ ይገባል።

በመልሶ ማቋቋም ስራም በክልልና ወረዳ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አቶ አመኑ አስታውቀዋል።

ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለህዝቡ እርቀ ሰላም መውረድ ሚናቸውን ከተወጡ የሃይማኖት አባቶች መካከል ቄስ ገበየሁ ከበደ በሰጡት አስተያየት ሠላም የሰው ልጆች መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢው ህዝብ ለሶስት ዓመታት ተረጋግቶ በቄየው መኖር አለመቻሉን ጠቁመው ይህ የጨለማ ጊዜ በእርቅ ሠላም አልባት በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው የባህል አምባሳደር አቶ ጠማሙ አርማዶ የኩስሜ ህዝብ የተፈጠረውን ግጭትና ቅራኔ በመተው ፊት ለፊት ተገናኝተው በባህላዊ መንገድ በይፋ ይቅር መባባላቸው የሚያስደስት መሆኑን ተናግረዋል።

በባህላቸው መሰረት ከእርቅ በኋላ መልሶ መጋጨት ስለማይኖር የቀድሞው አብሮነትና አንድነት ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ግጭት የሰውን ህይወትና ንብረት ከማጥፋት ሌላ ምንም ዓይነት ጥቅም እንደማያገኝ የተናገሩት ደግሞ የጋቶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታደሰ ጉይታ ናቸው።

የኩስሜ ህዝብ አንድ ባህልና ቋንቋ ባለቤት ቢሆንም በህዝቡ መካከል የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች በለኮሱት እሳት ከ17 የቤተሰብ አባላታቸው ጋር ለሶስት ዓመት ከቄያቸው ተፈናቅለው በችግር ማሳለፋቸውን አውስተዋል።

አሁን ላይ በህዝቡ መካከል የተፈጠረው ግጭት ረግቦ በእርቅ ሠላም እልባት በማግኘቱ ሁሉም ተረጋግተው የዕለት ተዕለት ህይወታችን ለመምራት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን ከግጭቱ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 50 ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ከወረዳው ሠላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም