በሃረሪ ክልል ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል -አቶ ኦርዲን በድሪ

68

ሀረር፣ ሚያዚያ 3/2013 ( ኢዜአ) በሃረሪ ክልል ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተከነወኑ የሚገኙ የድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ::

ክልሉን ወክሎ በአንደኛ ሊግ ምድብ ሁለት ውድድሩን በአንደኛነት አጠናቆ የዋንጫ ባለቤት ለሆነው የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ ዛሬ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶለታል።

በእውቅና አሰጣጡ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በዚህ ወቅት “ በማንኛውም የልማት የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ስራዎች ላይ እርስ በርስ ተደጋግፈን ከሰራን ውጤታማ መሆን ይቻላል”ብለዋል።

“የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ለዚህ ድል መብቃቱ ጥረት ካለ የተፈለገው ስኬት ላይ መድረስ እንደሚቻል በግልጽ የሚያሳይ ነው” ብለዋል:: 

በክልሉ የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶችም ይሄንን በመመልከት እና መልካም ተሞክሮዎችን በመቅሰም ለተሻለ ደረጃ እንዲተጉ ልምዶቻቸውን እንዲያካፍሉ አሳስበዋል። 

የከልሉ መንግስት እግር ኳስን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የስፖርት አይነቶችን ይበልጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያከናውነውን የድጋፍ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ያሲን ዩስፍ በበኩላቸው የክልሉ ካቢኔ ክለቡ ውጤታማ እንዲሆን 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር መመደቡ ክለቡ ከዚህ ቀደም የነበረበትን የበጀት ችግር ሙሉ ለሙሉ በመቅረፍ ለውጤቱም ማማር የአንበሳውን ድርሻ መወጣቱን ተናግረዋል።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽንም በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች ክልሉን የሚያስጠሩ ተተኪ ወጣቶችን የማፍራት ስራ በተጠናከረ መልኩ እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ስፖርት ቡድን ዋና አሰልጣኝ አሰግድ ሰይፉ በበኩሉ የእውቅና ሽልማቱ የሚያበረታታና ለተሻለ ስራም የሚያነሳሳ ነው ብሏል።

“ክለቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና የክልሉን ስም ለማስጠራት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን” ሲል ተናግሯል።

በእለቱም የእግር ኳስ ክለቡ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉ አካላት የዋንጫና የምስክር ወረቀት እንዲሁም ለእግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾችና አባላት የገንዘብ ሽልማት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እጅ ተበርክቶላቸዋል።

በአንደኛ ሊግ የሚሳተፈው የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ በ2013 የውድደር ዘመን በ1ኛና 2ኛ ዙር ውድድር 28 ነጥብ በመያዝ ውድድሩን በአንደኛነት ማጠናቀቁ እና የዋንጫ ባለቤት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም