በምእራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ ነዋሪዎች የጥፋት ሃይሎችን በማጋለጥ ከመንግስት ጋር እንደሚሰሩ ገለጹ

74

ነገሌ ሚያዚያ 3/2013 /ኢዜአ/ የገላና ወረዳ ነዋሪዎች በምእራብ ጉጂ ዞን ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የጥፋት ሀይሎችን በማጋለጥ ከመንግስት ጋር ተባብሮ ለመስራት ተስማሙ፡፡

ነዋሪዎቹ ትናንት በወረዳው ቶሬ ከተማ በሰላምና በአካባቢያቸው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባደረጉት የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ጉዳዩን አንስተው መክረዋል፡፡

የቶሬ ከተማ ነዋሪና የጉጂ ኦሮሞ አባገዳ ተወካይ አቶ ታደለ ባንታ የአንድነት የመረዳዳት የመቻቻልና የመከባበር ባህላዊ እሴቶቻችን በጥፋት ሃይሎች እየተሸረሸሩብን ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ ገላና ወረዳ በቅርቡ ለእርቅ በተቀመጡ በጉጂ ኦሮሞዎችና በኮሬ ህዝብ የሀገር ሽማግሌዎች ላይ የተፈጸመውም ጥቃት የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ዘላቂ ሰላም እንዲመጣና የህግ የበላይነት እንዲከበር የጥፋት ሃይሎችን በማጋለጥ ከመንግስት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ነው ያመለከቱት፡፡

የኮንፈረንሱ ተካፋይና የሃይማኖት መሪ ዮሀንስ አርባ በበኩላቸው የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ቅንጂታዊ አሰራር ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡

የጥፋት ተልእኮ ለማስፈጸም በሀገርና በህዝብ ላይ ኢሰብአዊ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት አስተማሪና ተገቢውን የቅጣት እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ውይይቱን የተካፈለው ወጣት ዳንኤል ቦርኬም ወጣቱን በሚያነሳሳ የጥላቻ ንግግር መመራት የለብንም ብሏል፡፡

የጥፋት ሃይሎችን በማጋለጥ የህግ የበላይነትን አክብሮ በማስከበር ሀገር የማዳን ስራ ከማንም በላይ የወጣቱ ድርሻ  እንደሆነም አብራርቷል፡፡

ውይይቱን የመሩት በገላና ወረዳ ብልጽግና ጽህፈት ቤት የህዝብ አደረጃጃት ሃላፊ አቶ ጉዮ ጨሪ "መንግስት ከዚህ በኋላ የጥፋት ሀይሎችን አይታገስም" ብለዋል፡፡

በመሆኑም የገላና ወረዳ ህዝብ ዘላቂ ሰላሙን  ለማረጋገጥ አጥፊዎችን  በማጋለጥ  የጀመረውን  የነቃተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ ከ200 በላይ የአበ ገዳ ተወካዎች፣ የሀገር  ሽማግሌዎች  የሀማኖት  አባቶች፣  ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም