የስንዴ መስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያ ነው….አቶ አገኘሁ ተሻገር

48

ባህር ዳር ኢዜአ ሚያዚያ 2/2013 ''በአማራ ክልል መስኖን በመጠቀም እየለማ ያለው ስንዴ በራስ አቅም ለምግብ እህል የሚውል ምርት በበቂ መጠን ማምረት እንደሚቻል ማረጋገጫ ነው'' ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

ርእሰ መስተዳደሩ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ፋግታ ላኩማ ወረዳ አመሽን ኩሪት ቀበሌ በኩታ ገጠም በመስኖ የለማ 290 ሄክታር ሰብል ጎብኝተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው ስንዴን በመስኖ የማልማት እንቅስቃሴ ውጤት የታየበትና ለቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትምህርት የተገኘበት መሆኑንም አመልክተዋል።

“በኢትዮጵያ ስንዴን በተሻለ ብዛትና ጥራት የማምረት ምቹ ሁኔታ ቢኖርም አቀናጅቶ ማምረት ባለመቻሉ በበርካታ ሚሊዮን ብር ስንዴ ከውጭ ሃገራት እንዲገባ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

ይህም ከአላግባብ የሚፈሰውን ውሃና ለም መሬት በመጠቀም በራስ አቅም በማምረት የምግብ አቅርቦት ክፍተቱን ማሟላት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ እየለማ ያለው ስንዴ ትልቅ ማሳያ እንደሆነ ገልፀዋል።

አርሶ አደሩ የጀመረውን ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት ርእስ መስተዳደሩ “የክልሉ መንግስት በሚችለው አቅም ከአርሶ አደሩ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል።

''በክልሉ 50 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ በምርጥ ዘር እጥረት ምክንያት 26 ነጥብ ስድስት በመቶውን ብቻ ማሳካት እንደተቻለ'' የገለጹት ደግሞ የግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ ናቸው።

መልማት ለቻለው መሬት ከውሃ መሳቢያ ሞተር ጀምሮ ለአርሶ አደሩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ ውጤታማ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በስምንት ዞኖች በ58 ወረዳዎች ከ13 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መስኖን በመጠቀም በስንዴ መሸፈን እንደተቻለም አስታውቀዋል።

“የክልሉን እምቅ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ በመጠቀም በስፋት ለማልማት የምርጥ ዘር ችግር ተግዳሮት እንደሆነ ገልጸው፤ በቀጣይ ችግሮችን በመፍታት አርሶ ደሩን በስፋት የማሳተፍ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

''መንግስት በሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ በማድረጋቸው አዲስ ተስፋ እንዲሰንቁ እንዳደረጋቸው የገለጹት'' ደግሞ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እያለሙ ያገኘናቸው የወረዳው አመሽ ሽንኩሪ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ትዛዙ የኔው ናቸው።

ከዚህ ቀደም አጃ እና ሽንኩርት በመዝራት ይተዳደሩበት የነበረው መሬታቸው ውጤታማ ሳያደርጋቸው እንደቆየም አስታውሰዋል።

ዘንድሮ መንግስት በሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት እስከ አሁን ስንዴ ዘርተውት የማያውቁትን መሬታቸውን ስንዴን በመስኖ በማልማት ከአስር እስከ 20 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።

'ከዚህ ቀደም በተለይ ውሃን በአግባቡ በመጠቀም ችግር መሬታቸውን በአግባቡ ለማልማት ሳይችሉ እንደቆዩ የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር አማረ አድማሴ ናቸው።

ዘንድሮ መንግስት የውሃ መሳቢያ ሞተር አርሶ አደሩን በክላስተር አደራጅቶ መስጠት መቻሉ ከራሳቸው አልፎ ለገበያ የሚተርፍ ስንዴ እንዲያለሙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ትናንት በተካሔደው ጉብኝት የክልልና የዞን እንዲሁም የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም